በምዕራብ ወለጋ አምስት ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ተዘጋጁ

71

ነቀምቴ ፣ሰኔ 1/2012( ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን በተመደበ ከ91 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በግንባታ ላይ ከነበሩ የትምህርት ቤቶች መካከል አምስቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ተዘጋጁ።

የዞኑ የትምህርት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ደስታ ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለተኛ ደረጃ ለሆኑት ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ማስፈጸሚያ የተመደበው በጀት በክልሉ የትምህርት ቢሮ ነው።

ተጠናቀው ለአገልግሎት የተዘጋጁት  በግንባታ ላይ ከነበሩ ስምንት ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሆኑ አመላክተዋል።

ግንባታቸው የተጠናቀቁት ትምህርት ቤቶች በኢናንጎ፣ ኮቦር፣ ሰዮ ኖሌ፣ አይራ እና  ድድቤ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

የቀሩት በጉሊሶ ፣  ቦጂ ጨቆርሳ እና ቆንዳላ ወረዳዎች እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ደስታ እስከ ነሐሴ 2012 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ግንባታቸው መቀጠሉን አስረድተዋል።

የትምህርት ቤቶቹ መገንባት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የደረሱ ተማሪዎች ወደ ሩቅ አካባቢ በመሄድ ለመማር በመገደድ ይገጥማቸው የነበረው ችግር ያቃልላል።  

የአይራ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ነሞምሣ አስፋው  በሰጡት አስተያየት 12 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት የአይራ ሁኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቆ በሚያዝያ ወር 2012 ዓ.ም  ለአገልግሎት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በአካባቢያቸው የተገነባው የቢቅልቱ ደበሶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቤተ ሙከራ እና  ቤተመፃሕፍት አካቶ  በፈረቃ 1ሺህ 200 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የሰዮ ኖሌ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ኢዶሣ ናቸው።

በሌላ በኩል  የነጆ ሁለተኛ ደረጃ ትምህረት ቤት የመማሪያ ክፍሎች ጥበትን ለመቀነስ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በመደበው በጀት 20 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውም ተመልክቷል።

የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት በምዕራብ ወለጋ ዞን ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 937 ትምህርት ቤቶች  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ላይ መቆየታቸውን ከዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም