መንግሥት የታገቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጉዳይ አልረሳውም

98

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) መንግሥት የታገቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጉዳይ የረሳውና የተወው እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ።

ከእገታው ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ይህን የተናገሩት በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ልዩ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው።

ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲሄዱ የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ በተመለከተ፣ መንግሥት የሚሰጠው ምላሽና የሰጠው ትኩረት አጥጋቢ አይደለም የሚል ጥያቄ ከምክር ቤቱ አባል ተነስቷል።

ለታገቱት ተማሪዎች ጉዳይ እልባት ለመስጠት ምን አይነት እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው? የሚልም እንዲሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌዴራል መንግስት ድርጊቱ ከተፈጸመ ጊዜ አንስቶ ሥራዎችን መስራቱንና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሚኒስትሮች ኮሚቴም ቦታው ድረስ በመሄድ ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ የታገቱትን ተማሪዎች ለማስፈታት አሰሳዎችን ማድረጉንና እንደሚባለው ሳይሆን መንግሥት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ ይገኙባቸዋል በተባሉ ሁሉም ቦታዎች በሚገኙ ቀበሌዎች በተደረገ አሰሳ የተገኘ ተማሪና ጉዳዩን እኔ ነኝ የፈጸምኩት ሲል ኃላፊነት የወሰደ አንድም ኃይል እንደሌለ አመልክተዋል።

ይሁንና እገታውን ያስተባበሩና ያቀነባበሩ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

መጀመሪያ ታግቼ ነበር ብላ ያለችውንና የሌሎች ተማሪዎችን ሰነዶች የያዙ ግለሰቦች ከያዙት ሰነድ ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

በቴክኒክ መረጃ የአንዳንዶቹ ታጋቾች ስልክ አንዴ አማራ ክልል ይገኛል፤ አማራ ክልል ሲፈለግ ጠፍቶ  ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ከዚያም ቤኒሻንጉል ሲፈለግ ኦሮሚያ እንደሚገኝና ይህም እንቅስቃሴ እንዳለ እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል።

ከእገታው ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች ታጋቾች ቤተሰቦቻቸው ጋር ገብተዋል የሚል መረጃ ይለቃሉ ይህን መሰረት አድርጎ ፍተሻ ሲደረግም የሚገኝ ተማሪ እንደሌለ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ቤተክርስቲያን ውስጥ ተለቀዋል ተብሎ ፍተሻ ሲደረግ እንደማይገኙና ጉዳዩ ተራ እገታ ነው ለማለት የሚያስቸግር እንደሆነም አክለዋል።

መንግስት በጊዜም፣ በገንዘብና በወታደር ኃይል አስፈላጊውን አሰሳ ማድረጉንና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተከታታይ ውይይቶች ማካሄዱንም ነው የተናገሩት።

በርካታ ግለሰቦች በመያዛቸው ምናልባት በታገቱት ተማሪዎች ጉዳይ ፍንጭ ሊገኝ እንደሚችልም ገልጸዋል።

መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልሰጠ አድርጎ ማየቱ ተገቢ እንዳልሆነና እስካሁን ከታገቱት ተማሪዎች 21ዱ እንዲለቀቁ መደረጉን አስታውቀዋል።

ከእገታው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ታግቼ ነበር የሚሉ እንዳሉና፣ መንግሥት የታገቱ ተማሪዎችን ሲያስለቅቅ ውሸት ነው አላስለቀቀም የታገቱ ተማሪዎች አሉ በሚል የሀስት መረጃ በማውጣት የፖለቲካ ጨዋታ የሚጫወቱም እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

መንግሥት የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግና ጉዳዩን ጊዜ የሚፈታው እንደሆነ አክለዋል።

መንግሥት ራሱ አግቶ ዝም እንዳለ አጋቾች እኛ አጋች ነን እያሉ ዝምታን እንደመረጠ ተደርጎ መታሰብ እንደሌለበትና ጉዳዩ በአንድ ጊዜ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችል እንዳልሆነም ገልጸዋል።

ይህን ጉዳይ የፖለቲካ አጀንዳ ያደረጉና ግጭት ለመፍጠር የሚሰሩ ኃይሎች እንዳሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት።

የታጋቾቹን ተማሪዎች ሁኔታ አስመልክቶ፣ የተደራጀና ተአማኒነት ያለው መረጃ የሚሰጥ አካል ቢኖርና መረጃውን ቢሰጥ፣ መንግሥት ወሮታውን እንደሚከፍልና በተባለው ቦታም አስፈላጊውን አሰሳ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

መንግሥት አስፈላጊውን መረጃ በማሰባሰብ የታገቱትን ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማገናኘት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኦሮሚያና በአማራ ከልል በመንግሥት የጸጥታ አካላትና በታጣቂዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አስመልክቶ ከ10 ቀናት በፊት ሪፖርት ማውጣቱ የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርቱን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም አምነስቲ ሪፖርቱን ሲያወጣ ያለው ዓላማ ምንም ይሁን ምን የህዝብ ሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱ መሆኑንና እርማት መወሰድ አለበት የሚለውን ጉዳይ መንግሥት መርምሮ ተገቢውን የህግ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

ጥሩ ሥራዎች እንደሚሰሩ ሁሉ ጥፋቶችም ሲኖሩ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሪፖርቱ ጭብጥ ሀሳብ ባለፈ ጉዳዩ ተጋኖ ሊታይ እንደማይገባውም ጨምረው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም