በወላይታና ቤንች ሸኮ የናዳ ፣ መሬት መንሸራተት እና ጎርፍ አደጋን ለመከላከል እየተሰራ ነው

57

ሶዶ/ሚዛን ሰኔ 1/2012 ( ኢዜአ) በወላይታ እና ቤንች ሸኮ ዞኖች ለመሬት መንሸራተት፣ ናዳና ጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የቅድመ መከላከል ስራ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።

የወላይታ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የዝናብ ወቅት ላይ የጎርፍ፣ መሬት መንሸራተትና ናዳ አደጋ በተደጋጋሚ ሲደርስ ቆይቷል።

የዚህ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አራት ወረዳዎችን መለየታቸውን አመልክተው፤ ይህም  የህዝብ ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ገደላማና ተዳፋት የበዛባቸው አካባቢዎች ጭምር ለእርሻ ስራ መዋላቸው አካባቢውን በማራቆቱ እንደሆነ አስረድተዋል።

የመሬት ጥበትን መሰረት በማድረግም ክፍት ቦታ ወዳለባቸው አካባቢዎች ተጋላጭ የሆኑ ቤተሰቦችን የማስፈር ፣ በተራቆተው ስፍራም  የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ ነው።

የተራቆተው መሬት ላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተው እየተተከሉ እንደሚገኝ ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

ባለፈው ወር  መጀመሪያ ላይ የጣለው ዝናብ ተከትሎ ከኪንዶ ኮይሻና ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳዎች በመሬት መንሸራተትና ጎርፍ አደጋ ምክንያት 359 ቤተሰቦች ተፈናቅለው እንደነበር አስታውሰው፤ ከእነዚህም 185 ወደ ቀድሞ ስፍራቸው መመለሳቸውንና " ከስጋት ነጻ ወደሆነ ስፍራ በቋሚነት የማዛወር ስራ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ወይዘሮ ኢትዮጵያ እንዳሉት ከኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ከተፈናቀሉ 102 ቤተሰቦች 76 የሚሆኑት ከዞኑ አስተዳደርና ከክልሉ መንግስት በተገኘ ድጋፍ ወደ ሌላ አካባቢ በማዛወር ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው፤ ቀሪዎቹንም እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ለማስፈር ታቅዷል።

በዞኑ ኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ጨረቼ ቀበሌ በጎርፍ ናዳ ምክንያት ተፈናቅለው እንዲቋቋሙ ድጋፍ ከደረገላቸው መካከል አርሶ አደር ሃናሬ ዳኖሌ ይገኙበታል።

አርሶ አደሩ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አሁን በቀበሌው ሌላ አካባቢ በተሰራላቸው ቤት መኖር መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በቤንች ሸኮ ዞን ሸዋ ቤንች ወረዳ ተደጋጋሚ የመሬት ናዳ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የቅድመ መከላከል ስራ  እየተካሄደ ነው።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተረፈ ስንቡል እንደገለጹት የወረዳው አብዛኛው አካባቢዎች ደጋማ በመሆናቸው በተደጋጋሚ የሚጥለው ዝናብ ተከትሎ በሚከሰት የመሬት መንሸራተትና ናዳ  በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ይደርሳል።

ዣዥ፣ ቢያክቦራ፣ ማዝ፣ መስከረም ፍሬና ሌሎች 11 ቀበሌዎች በወረዳው ለመሬት ናዳ ተጋላጭ እንደሆኑ መለየታቸውን  ጠቅሰው፤  ችግሩን በጊዜያዊና በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በቅርቡ በደረሰ የጎርፍ አደጋ 29 አባወራዎች ተፈናቅለው በትምህርት ቤቶች በጊዜያዊነት ተጠልለው ይገኛሉ።

በስጋት የተለዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር ከዞንና ከክልል የሚመለከታቸው አካላት ጋር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን  አቶ ተረፈ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም