ኤግዚቢሽኑ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና እንዲሰሩ ያስችላል ተባለ

63
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2010 የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያዘጋጀው ኤግዚቢሽንና የንግድ ትርዒት  የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና እንዲሰሩ እድል እንደሚፈጥርላቸው ተገለፀ። ምክር ቤቱ ያዘጋጀው 11ኛው ዓለም አቀፍ የግብርናና ምግብ ኤግዚቢሽን እንዲሁም 6ኛ የቱሪዝምና የጉዞ ንግድ ትርዒት በኢግዚቢሽን ማዕከል ዛሬ ተከፍቷል። በዚሁ ጊዜ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብራህቱ መለስ እንደተናገሩት ኤግዚቢሽኑና የንግድ ትርዒቱ የግብርናና የምግብ ውጤቶችን እንዲሁም የቱሪዝምን ዘርፍ ለማስተዋወቅ የሚረዳ ነው። ዝግጅቱ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች "ትስስር እንዲፈጥሩና በሽርክና እንዲሰሩ የሚያስችል" መሆኑን ነው የገለፁት። ከውጭ ለሚመጡ ኩባንያዎች አገሪቷን በማስተዋወቅ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል። ለአገር ገፅታ ግንባታ ካለው አስተዋፅኦ በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑንም ገልጸዋል። የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ በበኩላቸው በኤግዚቢሽንና ንግድ ትርዒቱ ላይ 70 የአገር ውስጥና 35 የውጭ ኩባንያዎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል። ኤግዚቢሽንና ንግድ ትርዒቱ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ተባብረው እንዲሰሩ የሚያስችል የልምምድ ልውውጥ የሚያካሂዱበት እንደሆነም ተናግረዋል። በኢግዚቢሽኑ ላይ የተሳተፉና ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩ ኩባንያዎች መኖራቸውን ለአብነት በማውሳት። ኤግዚቢሽኑ የገበያ ትስስር የሚፈጥርላቸውና ደንበኛ የሚያፈሩበት እንደሆነ የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች ገልፀዋል። ከተሳታፊዎቹ መካከል የአሚዩ ኢንጂነሪንግ የኢንዱስትሪና እርሻ መሳሪያዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሙዘሚል መሀመድ በኤግዚቢሽኑ መሳተፋቸው "የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዛቸው ነው" የገለፁት። 11ኛው የግብርናና ምግብ ኤግዚቢሽን እንዲሁም 6ኛው የቱሪዝምና የጉዞ ንግድ ትርዒት ከግንቦት 2 እስከ 6 ቀን በኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል። በኤግዚቢሽኑና ንግድ ትርዒቱ የኢትዮጵያ፣ ቻይና ፣ ግብፅ፣ ህንድ፣ ዮርዳኖስ፣ ኬንያ፣ ፓኪስታንና ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ኩባንያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም