በኦሮሚያ የልማት ፕሮጀክቶችን የማስፈጸም አቅም ከፍ ማለቱን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ገለጹ

57

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30/2012 (ኢዜአ) ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቃቸው የክልሉን መንግሥት የማስፈጸም አቅም ከፍ ማለቱን የሚያመለክት መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የከተሞች ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ። 


ምክትል ፕሬዚዳንቷ ይህንን ያሉት በገላን ከተማ ከ277 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተገነቡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በመረቁበት ወቅት ነው።

በገላን ከተማ የረጅም ጊዜ ችግር የነበረውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች 27 ፕሮጀክቶች በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።

ፕሮጀክቶቹን የመረቁት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንዳሉት በገላን ከተማ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት ፕሮጀክቶች ከዚህ ቀደም የሕዝብ የመልካም አስተዳዳር ጥያቄዎች የነበሩ ናቸው።

በከተማው የተሰሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና የገጠር መንገዶች የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት የኅብረተሰቡን የመልካም አስተዳዳር ጥያቄ ለመመለስና ተጠቃሚ ለማድረግ በመሥራት ላይ መሆኑንም ምክትል ፕሬዚዳንቷ አረጋግጠዋል።

የክልሉ መንግሥት በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ለሁሉም የከተማ አስተዳዳሮችና ወረዳዎች ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ዓመት እንዲጠናቀቁ መመሪያ መስጠቱ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት በክልሉ በዚህ ዓመት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተያዘው በጀት ዓመት ተጠናቀው ለአግልገሎት ክፍት በመሆን ላይ ናቸው ብለዋል።

ይህም የክልሉን መንግሥት የማስፈጸም አቅም ከፍ ማለቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የገላን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ እድሪስ በበኩላቸው በከተማዋ ዛሬ ተመርቀው ለአግልግሎት ክፍት የሆኑት ፕሮጀክቶች በከተማ አስተዳዳሩ 277 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ ናቸው ብለዋል።

ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑት 27 ፕሮጀክቶች መካከልም 22ቱ በዚህ ዓመት ተጀምረው የተጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፕሮጅክቶቹም ሙሉ በሙሉ በሚባሉ ደረጃ በማኅበር በተደራጁ ወጣቶች የተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በከተማው የወጣቱን የሥራ አጥነት ችግር ከመፍታት ረገድ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ያመለክታል ብለዋል።  

በዛሬው ዕለት ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል 28 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ፣ 10 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና በ71 ሚሊዮን ብር የተገነባ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ግንባታ መሆኑን አብራርተዋል።

የገላን ከተማ በ1990 ዓ.ም የተቋቋመች ሲሆን በኢንዱስትሪ ከተማነቷም ትታወቃለች።

በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ 149 የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች በሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን 80 የሚሆኑት ደግሞ ግንባታቸውን አጠናቀው በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገቡ መሆኑ ታውቋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም