ቋሚ ኮሚቴዎች ከተቋማት ጋር የስምምነት ቻርተር ለመተግበር እየተዘጋጁ ነው

86
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 ከተቋማት ጋር የስምምነት ቻርተር አሰራርን ለመተግበር እየተዘጋጁ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴዎች ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተጠሪ ተቋማትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሊሰሩ ያቀዱትን ግቦች  ቆጥረው  ለቋሚ ኮሚቴዎች እንዲስረክቡና ኮሚቴውም ቆጥረው እንዲረከቡ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል። የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ቋሚ ኮሚቴዎች እንደገለጹት፤ አቅጣጫውን ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወኑ ነው። የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ካሚል አህመድ እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ ለሚደረገው የድጋፍና ክትትል ውጤታማነት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል። ከዚህ በፊት በተካሄደው የዓመቱ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ቋሚ ኮሚቴው የሚከታተላቸው ተቋማት በተለይ በዋና ዋና ፕሮጀክቶች ላይ አሰራሩን ለመተግበር አቅጣጫ መቀመጡን አንስተዋል። ቋሚ ኮሚቴው በራሱ በኩል ዝግጅት ማድረጉን የገለጹት አቶ ካሚል በቀጣይ የሚሰጠውን አጠቃላይ አቅጣጫ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።  አቶ ካሚል እንደሚገልጹት፤ በስምምነቱ መሰረት ተቋማት ያቀረቡትን እቅዶች የመፈጸም ግዴታ አለባቸው፤ በማይፈጽሙት ላይ ደግሞ በምክር ቤቱ አፈጉባኤ በኩል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርብ ይሆናል። “በዕቅድ ሪፖርት ብቻ የሚደረግ ግምገማ ውጤታማ ላይሆን ይችላል'' ያሉት ሰብሳቢው ስምምነቱ ይህን ችግር የሚያቃልል በመሆኑ በቋሚ ኮሚቴው በኩል በጥሩ ሁኔታ ተቀባይነት እንዳገኘ ገልጸዋል። የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ካሴ በሪሁን በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን መነሻ ሀሳብ መሰረት በማድረግ በምክር ቤቱ የወረደውን አቅጣጫ እንደተቀበሉት ተናግረዋል። የስምምነት ቻርተሩን ስራ ላይ ለማዋል በኮሚቴ ደረጃ እየታየ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ቋሚ ኮሚቴዎቹ የሚከታተሏቸውና የሚደግፏቸው ተቋማት በ2011 በጀት ያቀዱትን ዕቅድ በአግባቡ ስለመፈጸማቸው የሚከታተሉበት ስርዓት እንዲፈጠር የጋራ ስምምነት ይፈራረማሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም