ኮሮናቫይረስን መከላከል ካልተቻለ በቱሪዝም ዘርፍ የሚያሳርፈው ተጽዕኖ የጎላ እንደሚሆን ተጠቆመ

71

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቱሪዝም መስክ የሚያሳርፈውን ተጽዕኖ ፈጥኖ መከላከል ካልተቻለ ዘርፉ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ማገገም እንደማይችል የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ መከሰቱን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ መጥፎ ጥላ እያጠላ መሆኑ ይታወቃል።

ወረርሽኙ አብዛኛውን የዓለም አገራትን ያዳረሰና የጎዳ በመሆኑ በተለይ በቱሪስት ፍሰት ላይ የራሱን ተጽዕኖ አሳድሯል።

ከሌሎች አገራት ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የሚመጡ ጎብኚዎችን በማስቀረቱ ከዘርፉ ይገኝ ነበረውን ገቢ እያሳጣ ነው።

እንደ ጣሊያንና ስፔን ያሉ የእውሮፓ አገራት ላይ ጭምር ጉዳት ማድረሱ የጎብኚዎች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እዲያሳርፍ አድርጓል።

ይህም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የቱሪዝም እንቅስቃሴው በእጅጉ እየተጎዳ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ዘርፉን ወደነበረበት ለመመለስ ሰፊ ጊዜ የሚወስድ ነው።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰርጸፍሬ ስብሃት እንደሚሉት ዘርፉ እንዲያገግም ለማድረግ በአገር ውስጥ ጎብኚዎች ላይ ሰፊ ሥራ መስራት ይገባል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቱሪዝም መስክ የሚያሳድረው ተጽዕኖ የጎላ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በተለይ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በአስጎብኝነትና መሰል የቱሪዝም ዘርፎች ላይ የተሰማሩትን እንደሚጎዳ አመልክተዋል።

የወረርሽኙን ዘርፈ ብዙ ጉዳት መከላከል ካልተቻለ የቱሪዝም ዘርፉ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ማገገም እንደማይችልም ኃላፊው አቶ ሰርጸፍሬ ተናግረዋል።

የቱሪዝም ዘርፉ መልሶ እንዲያነሰራራም ምሁራን በርካታ ጥናቶችን በማካሄድ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያፈላልጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ባደራጃቸው ሆቴሎች፣ በአየር መንገድና የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ የሚሰሩ የቢጫ ታክሲዎች ማህበር አባላት ዛሬ ደም በመለገስ ላይ መሆናቸውን አቶ ሰርጸ ተናግረዋል።

የማህበሩ አባላት በብሔራዊ ደም ባክንክ አገልግሎት በመገኘት ደም የመለገስ ተግባር የፈጸሙት ጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙን ተከትሎ በገጠመው የደም እጥረት ላስተላለፈው ጥሪ ምላሽ ለመስጠት መሆኑንም አመልክተዋል።

የቢጫ ታክሲዎች ማህበር በሥሩ በስድስት ንዑሳን ማህበራት የተደራጁ 450 አባላት ያሉት ሲሆን በዛሬው እለት ሁሉም ደም በመለገስ ተግባር እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።

ደም ሲለግሱ ኢዜአ ያነጋገርናቸው የቢጫ ታክሲ አሽከርካሪ አቶ ዳዊት አስራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ ሥራ ማቆማቸውን ተናግረዋል።

ይሁንና እንደአገር ወርርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ባይችሉም መንግስት ያቀረበውን ጥሪ ተከትለው በማህበራቸው በኩል ደም ለመለገስ መነሳሳታቸውን ገልጸዋል።

"ስራችን ለበሽታው ቀጥተኛ ተጋላጭ የሚያደርግ በመሆኑ እራሳችንን ጠብቀን ይህንን ጊዜ ማለፍ አለብን" ያሉት አቶ ዳዊት፣ ነገን ለማየት ዛሬ የጤና ባለሙያዎች የሚሉትን መስማትና ራስን መጠበቅ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።  

በተመሳሳይ ሙያ ላይ የተሰማሩት አቶ ተረፈ ይመር በበኩላቸው ደም ሲለግሱ የመጀመሪያ ጊዜያቸው መሆኑን ገልጸው ለመንግስት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ሲሉ ደም መለገሳቸውን አስረድተዋል።

የማህበሩ አባላት ከኮቪድ-19 በተጨማሪ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናቅረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም