ወረርሽኝን ከመከላከል በተጓዳኝ በአረንጓዴ ልማት ላይ መረባረብ ይገባል

54

ሐዋሳ፣ ግንቦት 30/2012 (ኢዜአ) ሃገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ከመከላከሉ በተጓዳኝ በአረንጓዴ ልማት ላይ መረባረብ እንደሚገባ በሁለተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀን የተሳተፉ አካላት አመለከቱ።

በሃዋሳ ታቦር ተራራ ላይ አረንጓዴ አሻራቸውን ለማሳረፍ ከተሳተፉት መካከል የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ  ከመሬት መራቆት ጋር ተያይዞ በየዓመቱ የሚያጋጥመንን የአየር መዛባት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ በችግኝ ተከላው ላይ መካፈላቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

"በተለይ በአንድነት ከተባበርን የኮቪድ ወረርሽኝን ከመከላከል ጎን ለጎን አረንጓዴ ልማታችንን ለማስቀጠል አቅም አለን" ብለዋል።

በዚህ ላይ ሁሉም መረባረብ እንዳለበትም አመልክተዋል።

ወረርሽኑን ለመከላከል መደበኛ ጥንቃቄዎች እንዳሉ ሆኖ በችግኝ ተከላ ወቅት አንዱ የመማሪያ መድረክ በማድረግ አጋጣሚውን መጠቀም  እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረጉ  እንቅስቃሴዎችና  መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎችን በአግባቡ ለመተግበር ጥረት ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሌላው ተሳታፊ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ድርቅንና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም  በሚደረገው የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በመሳተፏ መደሰቷን ገልጻለች።

"በአሁኑ ወቅት ሌሎች ስራዎችን ስንሰራ ርቀታችንን እንደጠበቅን ሁሉ ችግኝ ስንተክልና ስንኮተኩት ተመሳሳይ ጥንቃቄ በማድረግ ሊሆን ይገባል " ብላለች።

ከወረርሽኙ መከላከል በተጓዳኝ የዘንድሮውን 5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ለማስፈጸም በሃገር አቀፍ ደረጃ ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በመናበብ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፌዴራል የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ናቸው።

በችግኝ ተከላው ወቅት ከሚደረጉ ጥንቃቄዎች መካከል አንዱ ከአንዱ እንዳይገናኝ የመስመር ገደብ መቀመጡን ጠቅሰዋል።

"የቦታ ርቀትን  ከመጠበቅ ባሻገር አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ  የችግኝ ተከላውን በማካሄድ የተያዘውን እቅድ እናሳካለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም