ኢትዮጵያን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ህብረተሰቡን ማስተማርና የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል - ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ

66
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 ኢትዮጵያን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ብቸኛው መሳሪያ ህብረተሰቡን ማስተማርና የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በማታ፣ በርቀትና በክረምት መርሃ ግብር ያስተማራቸውን 9 ሺህ 724 ተማሪዎች ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ አስመርቋል። ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ብቸኛው መሳሪያ ህብረተሰቡን ማስተማርና ትምህርትን በስፋትና በጥራት ማዳረስ ነው። ''መንግስት ትምህርት የማህበራዊ ልማት ስትራቴጂ ዋነኛ ምሰሶ እንዲሁም የስልጣኔና የእድገት ቁልፍ መሆኑን በማመን ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በልማት መስኮች አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እውቀታቸውና በክህሎታቸው የዳበሩ ተማሪዎችን ለማፍራት ጥረት እያደረገ ነው'' ብለዋል። ችግር ፈቺ ስራዎችን የሚሰሩና በሳይንስ የተካኑ ተማሪዎችን ማብቃት መንግስት የያዘውን የሰው ሀብት ልማት ግብን ለማሳካት እየተሰራ ያለው ስራ ደረጃ በደረጃ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል። ዛሬ አዲስ አበባ ዩንቨርሰቲ ያስመረቃቸው ተማሪዎች ከአገሪቷ የልማት ፍላጎት አንጻር በቂ ባይሆንም ቀደም ካሉ ዓመታት ሲነጻጸር ተስፋ ሰጪና የተሻለ እንደሆነ ዶክተር ሙላቱ አስረድተዋል። የሴት ተመራቂዎች ቁጥር ከሌሎቹ ዓመታት ሲታይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና ለውጥ እያታየበት መሆኑን አመልክተዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶስተኛ ዲግሪ በብዛት ማስመረቅ መጀመሩና የዩኒቨርሲቲውን የእድገት ጉዞ የሚያሳይ በመሆኑ አመስግነው ''ብዙ አካል ጉዳተኞችን ተቀብሎ ማስተማሩ አገራዊ ግዴታውን ለመወጣት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ያሳያል'' ብለዋል። መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለአገሪቷ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ጥረት አስፈላጊ በሆነ መልኩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነበሩበትን ማነቆዎች ለመፍታት ያደረገው የአሰራርና የአደረጃጀት ማሻሻያ በአገሪቷ ልማት ውስጥ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም የመንግስት እምነት እንደሆነ አስረድተዋል። የትምህርት ጥራትና የትምህርት መስኮቹ ከአገሪቷ ፍላጎትና ከማህበረሰቡ ችግሮች ያላቸውን ተዛማጅነት በማረጋገጥ በየስራ ዘርፉ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች በተጨባጭ ለመለካት የሚያስችል አፈጻጸም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። የትምህርት ጥራትን ማምጣት ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን በማወቅ ሁሉም አካላት ለትምህርት ጥራት ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ''የምርቃቱ ደስታ ከተማሪዎች፣ ተመራቂ ቤተሰቦችና መምህራን ባለፈ ባለፉት ዓመታት የታዩ ውስብስብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በማለፍ ትልቅ ተስፋ ሰንቃ በከፍተኛ የልማትና የእድገት እንቅስቃሴ ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ ደስታው እጥፍ ድርብ ነው'' ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም