“ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ጸብ የመፍጠር ዓላማ የላትም”-- ጠቅላይ ሚንስትር ሀምዶክ

125

ግንቦት 28/2012(ኢዜአ) የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ ከሱዳን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ሀገራቸው ከጎረቤት ኢትዮጵያ ጋር ጸብ የመፍጠር ዓላማ የላትም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት በሱዳን በነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ወቅት የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ሀሰን አልበሽርን ከስልጣን ካወረደ በኋላ ለተቃውሞ አደባባይ የነበሩ ሰልፈኞች ወደ ቤታቸው እንዲገቡ በማስጠንቀቅ በወሰደው እርምጃ በርካታ ሰዎች የተገደሉበትን አንደኛ ዓመት መታሰቢያ በማስመልከት ከብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ የተለየ የድንበር ችግር ጉዳይ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ቀደም ሲልም በተለያዩ ጊዜያት የነበረ ነው ብለዋል፡፡

ሱዳን ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራት ጋር የድንበር ችግሮች ሲያጋጥሟት እንደነበርም አውስተዋል፡፡

“ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት በባህል ፣ በታሪክ እና በመልክአ ምድር እና በመልካም ጉርብትና የተሳሰረ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

እናም “በመካከላችን የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ ስልቶች አሉን” ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከሰሞኑ የተፈጠረው ክስተትም በዚህ መንገድ እንደሚፈታ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ ገልጸዋል፡፡

በትናንትናው እለት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን “ከሱዳን ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ሲናፈሱ የሰነበቱት ጉዳዮች የግድቡን አጀንዳ ወደ ድንበር አጀንዳነት ለማምጣት በማሰብ የተደረጉ” እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተለየ ለግጭት የሚዳርግ ምክንያት እንደሌለ እና የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ሁለቱ ሀገራትበድንበር አካባቢ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚፈ ቱበት የቆየ ስልት መኖሩን አውስተዋል፡፡

ሆኖም የሃገራቱን የጋራ ጥቅም በሚያስተሳስር መልኩ ግጭቱ እንዲፈታ የሃገራቱ ህዝብና መንግስታት ፍላጎት በመሆኑ ለዚህ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሱዳንና ኢትዮጵያ አመታትን የዘለቀ ጠንካራ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት አላቸው ያሉት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው ግጭት እንዲቀሰቀስ በማሰብ የተዛቡ መረጃዎችን በስፋት ለህዝቡ በሚያደርሱ የሶስተኛ ወገን ሚዲያዎች የሰሞኑ ሁኔታ ተጋንኖ እየተራገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል ሲል የዘገበው አል አይን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም