መምህራን ዕውቀታቸውን በማሳደግና መልካም ተግባር በመፈጸም ጊዜውን ማለፍ ይኖርባቸዋል ---የዩኒቨርሲቲ መምህራን

60

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2012 (ኢዜአ) በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርት የተቋረጠበትን ጊዜ መምህራን ዕውቀታቸውን በማሳደግና መልካም ተግባር በመፈጸም ማሳለፍ ይኖርባቸዋል ሲሉ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ገለጹ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዳሉት ወቅቱ የኮሮናቫይረስ የተስፋፋበት ቢሆንም መምህራን ጊዜውን እንደመልካም አጋጣሚ ወስደው ዕውቀታቸውን በተለያዩ መንገዶች የሚያዳብሩበት ሊሆን ይገባል።

በኢትዮጵያ ስቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማትና ምጣኔ ሀብት መምህር ዶክተር ካሣ ተሻገር እንዳሉት በዚህ ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት አገሮች ችግር ውስጥ ወድቀዋል።

"ኮቪድ-19 በሁሉም ዘርፍ ተፅዕኖ ያሳድራል" ያሉት ዶክተር ካሣ፣ በርካታ ዓለምአቀፍ ግንኙነቶችም በእዚሁ ምክንያት መቋረጣቸውን አስታውሰዋል።

ለአብነትም ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት የትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶች መቋረጣቸውን አመልክተዋል።

"በዚህም አገራት በሁሉም ዘርፍ ችግር ውስጥ ገብተዋል" ነው ያሉት ዶክተር ካሣ።

እንደ ዶክተር ካሣ ገለጻ ይህ ወቅት መምህራን በቤት ውስጥ የሚያሳልፉበት ጊዜ በመሆኑ አጋጣሚውን ዕውቀታቸውንና ዕይታቸውን ለማስፋት ሊጠቀሙበት ይገባል።

"መምህራን ቀደም ሲል ጊዜ በማጣትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ያላከናወኗቸውን ሥራዎች አሁን ያገኙትን ጊዜ ተጠቅመው ማከናወን ይኖርባቸዋል" ሲሉም ገልጸዋል።

ጊዜው እንዳይባክንም የመማሪያ ግብአቶችን ከማዘጋጀት ጀምሮ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ማሳለፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዙ በጎ ተግባራትን መፈጸም እንደሚገባቸው ዶክተር ካሣ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋዎችና ትምህርት ክፍል የስነ-ጽሁፍና የቋንቋ መምህር ቁልቁሉ ኢጆ በበኩላቸው፣ የተለያዩ የመገናኛ ዜዴዎችን በመጠቀም ለተማሪዎቻቸው ትምህርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በተለይ በማታው የትምህርት መርሀግብር ይማሩ ለነበሩ ተማሪዎች እንደ ኢሜይል እና ቴሌግራም ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመማር ማስተማር ሥራውን በማከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማትና ምጣኔ ሀብት መምህሩ ዶክተር ካሣ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራው እንዲጀመር መደረጉን ገልጸዋል።

በእዚህም "ዙም" የተባለ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቴክኖሎጂው በአንድ ጊዜ ከ100 በላይ ተማሪዎች ጋር በመገናኘት የመማር ማስተማር ሂደቱን በማከናወን ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ሌሎች መምህራንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፈው ለተማሪዎቻቸው ትምህርት እንዲሰጡ መክረዋል።

በኮቪድ-19 በሽታ ምክንያት በአገራችን ሁሉም የትምህርት ተቋማት የገጽ ለገጽ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም