በሐረሪ የአረንጓዴ ልማት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል... አቶ ኦርዲን በድሪ

66

ሐረር፣ ግንቦት 28/2012 ( ኢዜአ ) በሐረሪ ክልል በአረንጓዴ ልማት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም በ" ደከር "   አካባቢ ዛሬ ተጀምሯል።

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ  እንደገለጹት በክልሉ ባለፈው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ቀን ከተተከለው ከ190ሺህ በላይ ችግኝ ውስጥ  80 በመቶው ጸድቋል።

በክልሉ በዚህ የክረምት ወቅትም የኮሮና ቫይረስን ከመከላከሉ በተጓዳኝ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ይካሄዳል።

የክልሉ መንግስት የጀመረውን የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ኦርዲን አስታውቀዋል።

ችግኙን በመትከል እና በመንከባከብ አረንጓዴ አካባቢን  ለመፍጠር በሚካሄደው እንቅስቃሴ  ወጣቱ፣ ተማሪው እና አርሶ አደሩን ጨምሮ መላው የክልሉ ህብረተሰብ  ርብርብ እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"ችግኝ  መትከል ብቻ ሳይሆን እንዴት መጽደቅ እንዳለበት እቅድ አውጥተን እየሠራን እንገኛለን " ያሉት ደግሞ  የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ  አቶ ወርዲ ሐሺም ናቸው።

በዘንድሮ  የአረንጓዴ ልማት ሥራ በክልሉ ከሁለት ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ ችግች ለመትከል ታቅዷል።

የክልሉ ማህበረሰብ ችግኝ የመትከልና የማጽደቅ ልምድ ያለው በመሆኑ የተተከሉትንም  በመንከባከቡ ሥራ ላይ በትኩረት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በችግኝ ተከላ ሥራው ከተሳተፉት መካከል የኃይማኖት አባት ሼህ ከቢር ሙስጠፋ በሰጡት አስተያየት  "አያቶቻችን ያስረከቡንን አረንጓዴ ልምላሜ በአግባቡ ሳንይዘው በራሳችን ጥፋት አራቁተናዋል፤  አሁን ተራው ሠርቶ የማሳየት በመሆኑ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም" ብለዋል።

ችግኝን ተክሎና ተንከባክቦ  ለትውልድ ማስረከብ ስለሚገባ  ሁሉም  በትጋት እንዲሠራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አካባቢን በአረንጓዴ እጽዋት ማሳመር ንጹህ አየር እንድንተነፍስ የሚያደርግ በመሆኑ ሁሌም ችግኝ መትከልን ባህሌ አድርጌ እየሰራሁ ነው  ያሉት ደገሞ  የደከር አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ፈቲያ በከሬ ናቸው።

በክልሉ በዛሬው የአረንጓዴ አሻራ ቀን  የችግኝ ተከላ ፕሮግራም  ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም