የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ጎን ለጎን ደም የመለገሱ ተግባር እንዲቀጥል የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ጥሪ አቀረቡ

116

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ጎን ለጎን ደም የመለገሱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ጥሪ አቀረቡ።

የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ በብሔራዊ ደም ባንክ በመገኘት ደም ለግሰዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚህን ወቅት እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የደም ለጋሾች ቁጥር ቀንሶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ በተደረገው ተከታታይ የንቅናቄ ሥራ በአሁኑ ወቅት ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር መሻሻል አሳይቷል ብለዋል።

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከእለት ዕለት የለጋሾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፣ ተግባሩ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

"አሁንም ደም የሚያስፈልጋቸው ዜጎቻችን በሕክምና ውስጥ አሉ" ያሉት ሚኒስትሯ፣ ከዚህ አንጻር ደም የመለገሱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ የኮሮና ቫይረስ ከፈጠረው የጤና ቀውስ አንጻር በአሁኑ ወቅት ደም መለገስ ዋጋው ከፍ ያለ መሆኑን ነው ዶከተር ሊያ የተናገሩት።

ዜጎች ደም በሚለግሱበት ወቅት ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን ሊዘነጉ እንደማይገባም  መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም