"የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከኮሮና መከላከል ጥንቃቄ ጋር ተጣጥሞ ይካሄዳል" - አቶ ንጉሱ ጥላሁን

161

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2012(ኢዜአ)"የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃግብር ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከሚደረገው ጥንቃቄ ጋር ተጣጥሞ ይካሄዳል" ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታወቁ። 

የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃግብር ነገ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሀዋሳ አካባቢ ታቦር ተራራ ላይ ይጀመራል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መርሃ ግብሩን አስመለክተው ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ነገ የሚከበረውን የዓለም የአካባቢ ቀን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በይፋ እንደምታስጀምር ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ በፌዴራል ደረጃ በሀዋሳ ቢጀመርም በሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች ችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ሚጫ ወረዳ፣ በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወንጪ ወረዳ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን አንዱራ ወረዳና በጋምቤላ አኝዋክ ዞን በሚገኙ ወረዳዎችና በሌሎችም መርሃ ግብሩ ይካሄዳል ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የወቅቱ ስጋት እንደሆነና በዚሁ ሳቢያ እንቅስቃሴ ተገድቦ ቫይረሱን የመከላከል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው አቶ ንጉሱ ያስረዱት።

በወረርሽኙ ወቅት የምንከተለው መርህ "ምርት እናመርታለን ወረርሽኙን እንከላከላለን" የሚል በመሆኑ ወረርሽኙን እየመከትን የምርት ስራችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ችግኝ ተከላው  በጥንቃቄ  ተጣጥሞ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።

ችግኝ ተከላው በአካባቢ፣ በመንደር ፣በሰፈርና በቤተሰብ ተከፋፍሎ የሚካሄድና ችግኝ የሚተክሉ ሰዎችም ቫይረሱን ለመከላከል የተቀመጡ ግዴታዎችን በመተግበር እንደሚተክሉ ገልጸዋል።

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ፣ ርቀትን መጠበቅና ሌሎች የጥንቃቄ መርሆዎች ተጠብቀው የችግኝ ተከላው ይከናወናል ብለዋል።

በገጠሪቷ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ አርሶ አደሮች በግብርና ስራቸው ውስጥ የችግኝ ተከላውን ተግባር እንደሚያከናውኑም ጠቅሰዋል።

የችግኝ ተከላው ከተካሄደ ምርጫውን ማካሄድ ለምን አልተቻለም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሁለቱ ጉዳዮች የማይዛመዱና የማይገናኙ እንደሆኑ የተግባራቱን ባህሪይ ነጥሎ ማየት ይገባል ብለዋል።

ችግኝ ተከላውን በቤተሰብ፣ በአካባቢና በመንደር ተወስኖ ማድረግ የሚቻል እንደሆነና ምርጫ ውይይት፣ ክርክር፣ ቅስቀሳና በአጠቃላይ ብዙ ሰዎች የሚሰበሰቡበት እንደሆነም አክለዋል።

ችግኝ መትከል፣ አዝዕርት መዝራትና የግብርና ስራ ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጸው ይህን ማድረግ ካልተቻለ ለህዝቡ ምግብ የማቅረብ ሁኔታ ችግር ውስጥ ይገባል ብለዋል።

'ምርጫ ግን ለነገ ብለን ማቆየት የምንችለው ነገር ነው' ሱሉ ነው አቶ ንጉሱ ያስረዱት።

መንግስት ችግኝ ተከላውን ኮሮናቫይረስን ለመከላከል መወሰድ ካላባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ጋር አጣምሮ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አመልክተዋል።

ካለፈው ዓመት ጥንካሬዎችና ድክመቶች ተሞክሮ ተወስዶ የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በተቀናጀ፣ በተጠናና በተደራጀ መልኩ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የአምናው መርሃ ግብር ኢትዮጵያዊያን በጋራ ከቆሙ ተዓምር መፍጠር እንደሚችሉ ያሳዩበት ነው ብለዋል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር በህብረተሰቡ ውስጥ አሁንም ከፍተኛ መዘናጋት እየታየ መሆኑን አንስተውም መታረም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ቀን ህብረተሰቡ ራሱን ከቫይረሱ በመጠበቅ በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር አሻራውን እንዲያሳርፍም ጥሪ አቅርበዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል።

መንግስት ባለፈው ዓመት ከተተከሉት 4 ቢሊዮን ገደማ ችግኞች 84 በመቶ የሚሆነው መጽደቁን መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም