ኤጀንሲው የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

75

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 27 /2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከልና ምላሽ መስጠት የሚውል ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

የብሄራዊ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ወረርሽኙን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ያስችል ዘንድ አገር አቀፍ የሃብት ማሰባሰብ ሂደቱን ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዛሬው እለትም የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ያሰባሰበውን ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ለብሄራዊ የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክቧል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ ወረርሽኙ በኢኮኖሚ የዳበሩትን አገሮች ጭምር በእጅጉ ፈትኗል።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ኢኮኖሚና የተጠናከረ የጤና ስርዓት በሌላቸው አገሮች ችግሩ ይበልጥ ውስብስብ ሊሆን እንደሚችል መገመት አዳጋች እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም ሰፊው የማህበረሰብ ክፍል ወረርሽኙን ለመከላከል በቂ የሆነ ግብዓት ለማሰባሰብ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስትር እና የብሄራዊ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ዋና ጸሃፊ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ኤጀንሲው በራስ ተነሳሽነት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

''በቀጣይም ሁለተኛው ዙር የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር ላይ ሁሉም የድርሻውን በመወጣት ይህን ፈታኝ ወቅት በጋራ ማለፍ ይገባል" ብለዋል ሚኒስትሯ።

የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የሃብት አሰባሰብ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ የወረርሽኙ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፤ ''ድጋፉም በዚያው ልክ ሊጠናከር ይገባል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ተደራራቢነት ያለው ሃላፊነቱን እየተወጣ ባለበት በአሁኑ ወቅት ያደረገው ድጋፍ በአረዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ  በየእለቱ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ምላሽ ለመስጠት በተጀመረው ሁለተኛው ዙር የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፎው ሊጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም