የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች በ"ኦንላይን "ትምህርታቸው እየተከታተሉ ነው

71

አክሱም፣ ግንቦት 27/2012 (ኢዜአ) የድህረ ምረቃ ተማሪዎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸው እንዳይስተጓጎል ካሉበት ሆነው በ"ኦንላይን ቴክኖሎጂ " እንዲከታተሉ ማመቻቸቱን የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።

የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን በ"ኦንላይን ዕ እየተከታተሉ ያሉተ ከ600 በላይ  ተማሪዎች እንደሆኑ ተመልክቷል።

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ገብረመድሀን መዝገበ ለኢዜአ እንደተናገሩት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሂደት በ"ኦንላይን" እንዲቀጥል ተደርጓል።

የመማር ማስተማር ሂደቱ እየተከናወነ ያለው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንደሆነ ገልጸዋል።

የ"ኦንላይን "ትምህርት አሰጣጥ ሂደት የሚከታተል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የተዘጋጀው መተግበሪያ እየተከታተለ ይገኛል።

"የድህረ ምረቃ ፕሮግራም የመማር ማስተማር ሂደት ወጥ በሆነ መንገድ ለማከናወን የጊዜ  ገደቡ እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ ወጥቶለት እየተተገበረ ነው "ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተያዘው እቅድ መሰረት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ዘንድሮ  እንደሚያመርቅ ዶክተር ገብረመድሀን አስታውቀዋል።

ተመራቂዎችም ይህን   አውቀው ለአማካሪዎቻቸው የመመረቂያ ጽሁፋቸውን  በአግባቡ እንዲያዘጋጁ እና በኦንላየን ገለጻ ለማድረግ እንዲሰናዱም አመልክተዋል።

በዩኒቨርስቲው  የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር ሙሉጌታ ኪዳነ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ተደርጓል ብለዋል።

መምህራን ጥያቄዎች በማዘጋጀት እና "አሳይመንቶች"ን  በመስጠት ተማሪዎች  ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሎጂስቲክስ ትምህርት ክፍል የድህረ ምረቃ አንደኛ አመት ተማሪ ለአከ ነጋ በሰጠው አስያየት ዩኒቨርስቲው  የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ለመማር የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱ ተገቢ ነው ብሏል።

ዩኒቨርሲቲው  የመማሪያ መጽሓፍቶች እና "ሞጅል " በማዘጋጀት "በኦንላይን ቴክኖሎጂ " በመታገዝ  ትምህርታቸውን ለመከታተል እንዳስቻላቸው ገልጿል።

ትምህርት ክፍላቸው  የጋራ የሆነ  ቴሌግራም እና  የመልእክት መለዋወጫ መርብ "ኢ-ማይል" በመፍጠር ተማሪዎች ለትምህርት መጣቀሻ መጽሀፍትና ሌሎች ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የግል  ተንቀሳቃሽ ስልክና ላፕቶፕ በመጠቀም ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል እንዳስቻላቸው ተማሪ ለአከ ተናግረዋል።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስጋት ላይ ወድቆ የነበረውን የድህረ ምረቃ ትምህርታቸው  በቤታቸው  ሆነው በጽሑፍ እና በምስል የተዘጋጀውን ትምህርት በመከታተል ላይ እንደሆኑ የገለጸው ደግሞ የማኔጅመነት ትምህርት ክፍል የድህረ ምረቃ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ  ጸጋይ በርሀ ነው።

ኮሮና  ከመከሰቱ በፊት በ" ሶፍት ኮፒ " የትምህርት መርጃ ተዘጋጅቶ እንደደረሳቸው እና አሁን ደግሞ በ"ኦንላይን "ትምህርታቸው እንዲከታተሉ መደረጉን አመልክቷል።

ቫይረሱን ከመከላከሉ በተጓዳኝ  ትምህርቷ  ሳይስተጓጎል በ"ኦን ላይን "  ለመከታተል በመቻሏ መደሰቷን የገለጸችው ደግሞ የድህረ ምረቃ አንደኛ ዓመት የሂሳብ መያ ተማሪ ብርትኳን ዳዊት ናት።

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ከ600 በላይ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች  በ"ኦንላይን" ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም