በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ለውጥ እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ

66
ሰኔ 29/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲደግፉ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥሪያቸው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን  ወደ ሀገር ቤት የሚልኩትን ገንዘብ በባንክ በማድረግ ለሀገር ተጠቃሚነትና ህገወጥነትን ለመከላከል እንዲተባበሩ ጠይቀዋል። ኢትዮጵያውያኑ ከቀን ወጪያቸው ቢያንስ 1 ዶላር ለሀገራቸው ዜጎች ተጠቃሚነት እንዲያገለግል አስተዋፅኦ ቢያደርጉ ብዙ ለውጥ ማምጣት ይቻላልም ነው ያሉት። ከውጭ በእርዳታ የሚመጣ ገንዘብ ሀገሪቱን ሊያሳድግ ስላልቻለ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የቻሉትን አስተዋፅኦ በማድረግ እንዲተባበሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ ዲያስፖራዎች በትረስት ፈንድ የሚያስቀምጡት ገንዘብ ማንም ሳያጎድለው በገጠር ትምህርት ቤትና መሰል ልማቶችን ለመገንባት እንዲውል መንግስት በጥንቃቄ እንደሚሰራም ማረጋገጫ ሰጥተዋል። በውጭ የሚኖር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ አምባሳደር በመሆን የሌላ ሀገር ዜጎችን በማሳመን ኢትዮጵያን እነዲጎበኙ በማድረግ የቱሪዝምን ዘርፉ የሀገሪቱን እድገት እንዲደግፍ ትብብር እንዲያደርጉም ነው የጠየቁት። ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን በመስራት አጥፊዎችን በመገሰፅ ለሀገራቸው ቀና ስራ መስራት ይገባቸዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። በውጭም በሀገር ውስጥም ያሉ ምሁራን ልምድና ክህሎታቸውን በማካፈል መንግስት የጀመራቸው ፕሮጀክቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ሊተባበሩ ይገባል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ባለሃብቶች ስራ እድል እንዲፈጥሩና ግብር መክፈል ግዴታቸው ብቻ ሳይሆን የሞራል ልዕልናቸው ማረጋገጫ መሆኑን በመገንዘብ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገትና ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባልም ነው ያሉት። የመንግስት ሹሞች ሌብነትን በመጠየፍ፣ ቀን ከሌሊት በመስራት የ2011 በጀት ዓመት የተሳካ እንዲሆን ከምንም በላይ በንቃት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም