ያልተገባ የካሣ ጥያቄ በባሕርዳር ከተማ የውኃ ፕሮጀክቶች ላይ ጫና አሳድሯል--የክልሉ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ

57

ባሕርዳር ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) ያልተገባ የካሳ ክፍያና የአሰራር ክፍተት የባህርዳር ከተማ የንጹሕ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ጫና መፍጠሩን የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ገለፀ።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የልዑካን ቡድን በከተማዋው እየተገነቡ ያሉ የውኃ ፕሮጀክቶችን ጎብኝቷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት የከተማዋን የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት ተደራሽ ለማድረግ በ590 ሚሊዮን ብር የሁለት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል በባሕርዳር ዙሪያ ወረዳ ወገልሳ ቀበሌ በ13 ኪሎሜትር ርቀት በ93 ሚሊዮን ብር እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት በወሰን ማስከበር ምክንያት ለአንድ ዓመት ሊዘገይ ችሏል።

"ፕሮጀክቱ የአንድ ዓመት የጊዜ ውል ኖሮት በኅዳር ወር 2012 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን አሁን ላይ ግንባታው 50 በመቶ መድረስ ሲገባው ከ20 በመቶ በላይ መብለጥ አልቻለም" ብለዋል።

"ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ካሣ የማይገባውን አርሶ አደርና የወል መሬቶችን ጭምር ያለአግባብ ካሣ እንዲከፈላቸው በደብዳቤ በማዘዝ አላስፈላጊ ወጪ እንዲወጣ እያደረጉ ይገኛል" ብለዋል።

ሌላው በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ በጃፓን መንግሥት ድጋፍ በ500 ሚሊዮን ብር እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት ሲሆን 174 ሺህ ሕዝብን ለ20 ዓመታት የንጹሕ ውኃ ፍላጎት ማርካት የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል።

"አራት ሚሊዮን ሊትር ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ታንከርን ጨምሮ የተለያዩ ጥልቅ ጉድጓዶችን በማካተት ግንባታው እየተከናወነ ያለው ይህ ፕሮጀክት በስምንት ወራት ውስጥ የግንባታውን 39 በመቶ ማከናወን ተችሏል" ብለዋል።

የሁለት ዓመት የግንባታ ጊዜ ውል ያለው ሲሆን ተመሳሳይ የወሰን ማስከበርና የተለያዩ የግብአት አቅርቦት ችግሮች ፈተና መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተቋማቱ ግንባታ በወሰን ማስከበር ችግር እንቅፋት እየገጠማቸው በመሆኑ የክልሉ ከፍተኛ አመራር ባመነበት አካሄድ ችግሩን ለማስተካከል በማሰብ ጉብኝቱ መካሄዱንም ኃላፊው አስታውቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው እንደገለጹት የባሕርዳር ከተማ ዙሪያ በውኃ ተከባ ሕዝቡ በንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት እየተሰቃየ መሆኑን አሳሳቢ ነው።

ይህንን ችግር ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለግል ጥቅም ሲባል የሚያደናቅፍ አመራርም ሆነ ባለሙያ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

ካሣ ለሚያስፈልጋቸው የመሬት ባለይዞታዎች ተገቢውን ካሣ መክፈል አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ካሣ ሳይገባቸው ለሕገወጥ ቤቶች ካሣ የመክፈሉ ጉዳይ አስቸኳይ እርምት እንዲደረግበትም ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግሥት የውኃ ተቋማትን በአግባቡ ለመምራት አዳዲስ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኅብረተሰቡም ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመጸየፍ ሊያጋልጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚሁ የአንድ ቀን ጉብኝትም ርዕሰ መስተዳደሩን ጨምሮ የቢሮ ኃላፊዎችና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተገኝተዋል።

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት 72 በመቶ እንደሆነ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም