አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሴቶችና ህጻናት ከ120 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

56

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ከቻይልድ ፈንድ ያገኘውን 120 ሺህ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አነስተኛ የገቢ ምንጭ ላላቸው ሴቶችና ህጻናት አስረከበ።

በነዚህም 120 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና የወተት ድጋፍ ተደርጓል።

የወረርሽኙ መከሰት ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በእጅጉ እየጎዳ መሆኑን የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የህጻናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡመድ ተናግረዋል።

ወረርሽኙ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎም ተቋሙ ከተለያዩ አካላት ድጋፍ ማግኘቱ ሁሉንም ለመድረስ ያስቻለው መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ያሉ ልጆች ወጪያቸው የሚሸፈነው በተለያዩ አገራት የሚኖሩ በጎ አድራጊዎች በሚያደርጉት ድጋፍ መሆኑን አስታውሰው፣ አሁን የተከሰተው ወረርሽኝ ለችግር ተጋላጭ እያደረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ የፕሮግራምና ስፖንሰርሺፕ ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ጀማል ድጋፉ ለ170 ሴቶችና ከሰባ ለሚበልጡ ህጻናት እንደሚውል ተናግረዋል።

በክልሎች ተመሳሳይ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የሴቶችን የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ችላ እንደሚልና ለሌሎች አካላት አርአያ ለመሆን ሲባል ድጋፉ መደረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም ድጋፉ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የተከሰተው ወረርሽኝ እስኪያልፍ ድረስ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጋራ መረባረብና ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም ሚኒስቴር ዴኤታዋ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም