የኢትዮጵያና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተወያዩ

53

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሶስትዮሽ ድርድር ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ።

የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ እና ልዑካቸው ከሱዳን አቻቸው ፕሮፌሰር ያሲር አባስ ሞሐመድ እና ልዑካቸው ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ምክክር አድርገዋል።

ውይይቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሶስትዮሽ ድርድር ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መሆኑ ተገልጿል።

አጀንዳውም የሶስትዮሽ ድርድሩ እንደገና የሚጀምርበት፣ ስለሚከናወንበት የስነ-ስርዓት ጉዳዮች እና ግድቡን በተመለከተ የአገራቱ ዋና ዋና ጉዳዮች እና ሃሳቦችን የተመለከተ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ሁለቱ ወገኖች የሁለትዮሽ ውይይቶችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የሶስትዮሽ ስብሰባው በቶሎ እንዲጀመር ስለማመቻቸት መስማማታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች ከድርድሩ ጋር የተያያዙ ያልተፈቱ ዋና ዋና ጉዳዮችን በተመለከተም ሃሳብ የተለዋወጡ መሆናቸውን ከኢፌዲሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያለመክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም