ለድሬዳዋ ሥራ አጥ የገጠር ወጣቶች ትራክተሮች ተሰጡ

69

ድሬዳዋ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃና ማዕድን ኢነርጂ ቢሮ በገጠር የሚስተዋለውን የወጣቶች ሥራ አጥነት ለመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ በ1ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የተገዙ ሁለት ትራክተሮች ለወጣቶች መስጠቱን ገለፀ ።

ትራክተሮቹ የተሰጣቸው ወጣቶች እርሻቸውን በዘመናዊ መንገድ በማከናወን ህይወታቸውን ለመለወጥ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ግብርና ፣ ውሃ  ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እንደገለፁት ትራክተሮቹ የተገዙት የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ከተመደበው በጀት ነው።

 ቢሮው በ1ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የገዛቸውን ሁለት ትራክተሮች በዋሂልና ለገኦዳ ጉኑንፈታ ቀበሌዎች በማህበር ለተደራጁ 40 ሥራ እጥ ወጣቶች ተሰጥቷል።

ቢሮው  የስራ አጥ ወጣቶችን ችግር ለመቅረፍ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ትራክተር ከተሰጣቸው መካከል 20 አባላት ያሉት የዋሂል ገጠር ቀበሌ ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ናስር አህመድ ለኢዜአ እንደተናገረው አብዛኛዎቹ የማህበሩ አባላት በግብርናና በሌሎች ሙያዎች በዲፕሎማ ተመርቀው ያለ ሥራ ተቀምጠው የነበሩ ናቸው ።

በተሰጣቸው ትራክተር አነስተኛ መሬታቸውን በዘመናዊ መንገድ በማልማት ሙያቸውን በሥራ ላይ ሊያውሉት ዝግጁ መሆናቸውን ሰብሳቢው ተናግሯል።

በተጨማሪ ትራክተሩ በተመጣጣኝ ክፍያ የሌሎች አርሶ አደሮችን መሬት በማረስ ጊዜያቸውና ጉልበታቸውን እንዲቆጥቡ ከማድረግ ባሻገር ለማህበሩም የገቢ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል እንጠቀምበታለን ብሏል።

የለገኦዳ ጉኑንፈታ ቀበሌ ወጣቶች ሰብሳቢ ወጣት ሙራድ ቃሲም በበኩሉ ከአላጌ ግብርና ኮሌጅ ተመርቆ ያለ ሥራ 3 ዓመት መቀመጡን ተናግሮ አሁን በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ በቁርጠኝነት በመስራት ለሌሎች ሥራ እጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተናግሯል፡፡

በማህበር የተደራጁ ሁለቱም የወጣት ማህበራት እያንዳዳቸው 100 ሺህ ብር መቆጠባቸው ተናግሮ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በድሬዳዋ ከተማ ሌሎች የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ለመጀመር የሚያስችልና  ዕቅድ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

መንግስት የወጣቱን የሥራ አጥነት ችግሮች ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን በመግለፅ በቀጣይም እራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ እገዛው እንዳይለያቸው ጠይቀዋል ።

ትራክተሮቹ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ማረሻና ጋሪዎች ሊሟሉላቸው ይገባል ያለው ደግሞ ያሲን ጀማል ነው፡፡

ወደፊት ለሌሎች ወጣቶች አርአያ መሆን የሚያስችል ተግባር ከማከናወን በተጨማሪ ለሌሎች ወጣቶች ሥራ እንፈጥራለን ብሏል፡፡

የወጣቶቹ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና ትራክተሮቹ ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማረሻና ጋሪ በፍጥነት እንደሚገዛላቸው የቢሮው ኃላፊ ከሰጡት ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም