ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች በደረቅ ወደቦች ዘንድ ተገቢውን አገልግሎትና መስተንግዶ እንዲሰጣቸው ተጠየቀ

69

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2012(ኢዜአ) ከጅቡቲ የሚመላለሱ የደረቅ ጭነት ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች በደረቅ ወደቦች የሚሰጣቸው መስተንግዶ እንዲሻሻል የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ጠየቀ።

የሰመራ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ አሽከርከሪዎች የኮቪድ 19ን ስጋት ባቀለለ አግባብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ የወጭና ገቢ ንግዷን የምታሳለጥበት ከጅቡቲ ባህር ወደብ እስከ መዳረሻ የኢትዮጵያ ደረቅ ወደቦች ያለው መንገድ ለተሽከርካሪም ሆነ ለአሽከርካሪዎች ደህንነት ሁሌም ስጋት እንደማይለየው ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች የሚያነሱት ሮሮ ነው።

ከመንገዱ ብልሽትና ከፍተኛ ሙቀቱ አስቸጋሪነት ባለፈ ደግሞ በደረቅ ወደቦች በኩል የሚስተዋለው አሰራር መጉላላትን እንደሚፈጥር ቅሬታቸውን ያነሳሉ።

አሁን ላይ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ደግሞ ነገሩን አብሶ፣ ለበሽታው ተጋላጭነት በማያጋልጥ መልኩ እንደማይስተናገዱ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌደሬሽን ለኢዜአ ገልጿል።

የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ይርጋለም ሠፋኒ እንዳሉት በደረቅ ወደቦች ዕሁድና ቅዳሜ ስለማይሰራ በየዕለቱ በወደቦች የሚደርሱ አሽከርካሪዎች መጉላላት እንደሚደርሰባቸውገልጸዋል።

በተጨማሪ በወደቦቹ በኮንቴይነር ማንሻ ክሬኖች ብልሽት ሰበብ መጉላላት እንዳለም ያነሳሉ።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የውሃ አቅርቦት በወደቦች በኩል እጥረት እንዳለ ጠቅሰው፤በበረሃው ውስጥ ለሚሰሩ አሽከርካሪዎች የውሃ አቅርቦት ጉዳይ በዘላቂነት መፈታት ያለበት ተግዳሮት እንደሆነ ገልጸዋል።

አሽከርካሪዎች የምግብ መስተንግዶም በወደቦቹ ሊከለከሉ አይገባም ይላሉ።

በደረቅ ወደብ ሠራተኞች ዘንድ አሽከርካሪዎች ሁሉ ወረርሽኙን እንደሚያዛመቱ አድርጎ መመልከትና ማግለል እንደማይገባ አቶ ይርጋለም ተናግረዋል።

በመሆኑም በወደቦቹ የሚሰጠው መስተንግዶና አገልግሎት የአሽከርካሪዎችን ሞራልና ክብር በጠበቀ አግባብ እንዲስተካከል ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ከስምንት ያላነሱ ደረቅ ወደብና ተርሚናሎች ያሏት ሲሆን፣ ከጅቡቲ በቅርበት ላይ ከሚገኙት ወደቦች መካከል የሰመራና የድሬዳዋ ደረቅ ወደቦች ቀዳሚዎቹ ናቸው።

የሰመራ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቤኩማ ቲጫ ለኢዜአ በሰጡት ምላሽ ኮቪድ 19 ወረርሸኝን በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ ለድርጅቱ ሠራተኞችና ደንበኞቹ ቫይረሱ እንዳይዛመት ግብዓቶች ለማሟላት ጥረት መደረጉን ይናገራሉ።

የወረርሽኙ ስጋት አንዱ የድንበር ተሻጋሪ መኪና አሽከርካሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ለዚህም ስጋቱን ለመቀነስ፣ ለአሽከርካሪዎችና ለሠራተኞች ደህንነት አሽከርካሪዎች ከበር ላይ ሰነዶቻቸውን ለሰራተኞች አስረክበው ጉዳያቸው በሠራተኞች በኩል የሚፈጸምበት ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።

አሰራሩ አሽከርካሪዎቹ አካላቂ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲስተናገዱ ለማግለል እንዳልሆነም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የወደቡ የምግብ አገልግሎት አካላዊ ርቀታቸውን በጠበቀ መልኩ ለመስጠት እንጂ፤ ክልከላ እንዳልተደረገ ገልጸዋል።

ከቦታው በረሃማነትና ከወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረረሽኝ ጋር በተያያዘ የውሃ አቅርቦት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ያምናሉ።

በደረቅ ወደቡ የውሃ አቅርቦት እስካሁን በቦቲ እየተመላለሰ እንደነበር አስታውሰው፣አሁን ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከአፋር ክልል መንግሥት ጋር ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም