በጠረፋማ አካባቢዎች ቫይረሱን የመከላከል ሥራ መጠናከር ይኖርበታል ... ሰላም ሚኒስቴር

70

ጋምቤላ ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ጠረፋማ አካባቢዎች ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና የስደተኞችን ፍልሰት በመቆጣጠር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን የመከላከሉ ስራ መጠናከር እንዳለበት የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሰላም ሚኒስቴር የሚመራው የጠረፋማ አካባቢዎች የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ-ሃይል በጋምቤላ ክልል ወረርሽኙን ለመከላከል እየተካሔዱ ያሉ ስራዎችን ጎብኝቷል።

የሰላም ሚኒስትር ዲኤታና የግብረ-ሃይሉ ሰብሳቢ ዶክተር ስዩም መስፍን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በክልሉ ጠረፋማ አካባቢዎች ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና የስደተኞችን ፍልሰት መቆጣጠር የቫይረሱን ስርጭት የመከላከል ስራ ወሳኝ ነው።

ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰንና ከፍተኛ የስደተኛ ቁጥር ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለወረርሽኝ ሊጋለጥ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም ተናግረዋል።

"በመሆኑም የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በተላለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት የመውጫ መግቢያ በሮችን በመዝጋት ህገ-ወጥ ዝውውሩንና የስደተኞችን ፍልሰት የመገደቡ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት"ብለዋል። 

በተለይም በደቡብ ሱዳን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት እየተበራከተ የመጣውን የስደተኞች ፍልሰት መገደብ ካልተቻለ ለወረርሽኙ የመጋለጥ ሁኔታው ከፍ ሊል እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ባለፈው ሳምንት ብቻ ወደ ክልሉ ገብተዋል የተባሉ 3ሺህ 800 ያክል ስደተኞች ከለይቶ ማቆያ ወጥተው ወደ ማህበረሰቡ እንዳይቀላቀሉ የተጠናከረ ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት ወረርሽኙን ለመከላከል የሃብት ማሰባሰብ ስራዎችን ጨምሮ እያከናወናቸው ያሉት የቅድመ መከላከል ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ በበኩላቸው በመስክ ምልከታው የክልሉ መንግስት ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ በሁሉም ዘርፎች እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በክልሉ በእስከ አሁን ሒደት በቫይረሱ የተያዘ ሰው ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ የመዘናጋት ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በተለይም አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅ ጀምሮ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የመጠቀም ክፍተቶችን ለማስተካከል የተጠናከረ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

"እንደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተለይም የህክምና መሳሪያዎችንና ሌሎች ግብዓቶችን በመደገፍ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ" ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው በጉብኝቱ የተለዩ ክፍተቶችን በማረም ወረርሽኙን ለመከላከል የተጀመሩ ጥረቶች ይበልጥ በትኩረት እንደሚሰራባቸው ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ለጀመራቸው ስራዎች መሳካትም በፌዴራል መንግስት የተጀመሩ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ግብረ-ሃይሉ ላለፉት ሁለት ቀናት ባካሔደው ጉብኝት ላይ የክልሉና የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም