የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የፊታችን ዓርብ ይጀመራል

81

አዲስ አበሀባ፣ ግንቦት 26/2012(ኢዜአ) የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የፊታችን ዓርብ እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት  መልዕክት እንዳመለከቱት  የዚህ ዓመት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ግንቦት 28 ቀን 2012 ይጀመራል።

'ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር እየተፋለምን ቢሆን፣ 5 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ዕቅዳችንን እናሳካዋለን'' ሲሉም ጽፈዋል።

እያንዳንዱ ቤተሰብ አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ አሻራውን የሚያሳርፍበት መንገድ  እንደሚመቻች አሳስበዋል።

''ባለፈው ዓመት እያንዳንዳችን አገራዊ ጥሪውን ተቀብለን፣ ያቀድነውን አሳክተናል'' ብለዋል።

በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት አራት ቢሊዮን  ችግኞች ተተክለዋል።ሐምሌ 22 ቀን 2012 በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን ብቻ  ከ300ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል።

አምና ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ 84 በመቶ  ጸድቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ''በአካል ተራርቀን፤ ንጽሕና ጠብቀን፣ እርስ በርስ ተረዳድተን- ኢትዮጵያን ከኮሮና እንታደግ!'' በማለት መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም