የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ አደረገ

67

ድሬዳዋ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ከ142 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የምግብና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ አደረገ።

ከድጋፉም መካከል ልዩ ልዩ ምግብ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ ሳኒታይዘርና ሣሙና ይገኙበታል።

የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት "የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከልና ተፅዕኖውን ለመቀነስ ተቀናጅቶ መሥራትና መደጋገፍ ይገባል" ብለዋል።

በድሬዳዋ የሚስተዋለውን የመደጋገፍ ባህል ራስን ከኮሮና ለመጠበቅ የሚበጅ በመሆኑ መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ነዋሪው ለዘመናት ሲጠቀምበት የቆየው የጋራ ኑሮ ለጊዜው በመተው በጤና ባለሙያዎችና መንግሥት የሚተላለፉትን መመሪያዎች በማክበር ራሱንና ቤተሰቡን እንዲጠብቅ ብለዋል።

ወጣቶች ባላቸው አቅም ኅብረተሰቡን ከወረርሽኙ ለመከላከል እያደረጉ ያለውን ጥረት አድንቀው ይኸው በጎ ተግባር መጠናከር እንዳለበትና ተቋማትም ሊደግፏቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

ድጋፉን የተረከቡት  የድሬዳዋ ተከማ አስተዳደር ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ከሪማ ዓሊ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው "በኮሮና ወረርሽኝ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ይሰጣል" ብለዋል።

ቢሮው በገጠርና ከተማ ትኩረት ሰጥቶ ኅብረተሰቡ ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ እያስተማረ መሆኑንም ገልጸዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ወጣቶችን የማሳተፍና የማብቃት ዳይሬክተር አቶ እስክንድር አህመድ በበኩላቸው "ከ500 በላይ ወጣቶች ቫይረሱን ለመከላከል በማስተማርና በመቀስቀስ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል" ብለዋል።

ወጣቶቹ ሕዝብ በብዛት በሚገኝባቸው የገበያ ሥፍራዎች እጅ በማስታጠብ፣ አካላዊ ርቀት እንዲጠበቅ በማድረግ በኩል አበርታች ሥራ እያከናውኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ  ሕይወት ኃይሉ የተመራው የልዑካን ቡድን ለተመሳሳይ ድጋፍ  ዛሬ ወደ ሐረር አቅንተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም