ኮሚሽኑ ወንጀሎችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል ቅድመ ጥናት በማድረግ ወደ ሥራ ገብቷል

95

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) ወንጀሎችን ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ጥናት በማድረግ በሁሉም ክልሎች ወደ ሥራ መግባቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚታዩ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን የተመለከተ ቅድመ ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።

ከአሁን ቀደም የተፈፀሙ ወንጀሎችን በማጣራት፤ ወንጀሎች በሚፈጸሙበት ወቅትና ቦታ የመከላከልና ቅድመ መከላከል ሥራዎችን ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን እየሰራን ነው ብለዋል።

ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለህግ የማቅረብ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልፀዋል።

ወንጀሎች በባህሪያቸው፣ በፈፃሚዎቹ አካላት፣ በወንጀሉ ክብደትና ቅለት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይቀያየራሉ ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ይህን ቀድሞ መከላከል የሚያስችል በቂ ጥናት መደረጉን ነው ያብራሩት።

በተለይም እንደ ዝርፊያ፣ ግድያና ሌሎች የተደራጁ ወንጀሎችን እንደ አገር ወጥ በሆነ መልኩ ቀድሞ ለመከላከል እንዲያስችል በተጠናው ጥናት መሰረት ለሁሉም ክልሎች እቅድ ተልኳል ነው ያሉት።

ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከልም ይሁን ከተፈጸሙ በኋላ፤ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ወደ ሕግ ለማቅረብ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንና ለዚህም ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች በተለያዩ መንገዶች እየተከናወኑ እንደሆነ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም