የሠላም ሚኒስቴር ለፀጥታ ኃይሎች የኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ ሰጠ

93

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የሠላም ሚኒስቴር ለክልሎች፣ ለፌዴራልና ለከተማ አስተዳደር የፀጥታ ኃይሎች የኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ሚኒስቴሩ በግዥና ከተለያዩ አካላት በድጋፍ ያሰባሰባቸውን 63 የሙቀት መለኪያ፣ 45 የፕላስቲክ ሙሉ ልብስ፣ 68 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ ከ5 ሺህ በላይ የእጅ ጓንትና 1 ሺህ 600 ሊትር ሳኒታይዘር ዛሬ አስረክቧል።  

የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል "በየደረጃው ያሉ የጸጥታ ኃይሎች አሁን የገጠሙንን ችግሮች በመከላከል ሂደት ልክ እንደ ጤና ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ተሳትፎ ያላቸው ናቸው" ብለዋል።

ድጋፉ የጸጥታ ኃይሎች የቫይረሱ ስርጭት እንዳይሰፋ እየሰሩ ያሉትን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ በብቃት እንዲወጡ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

የችግሩ መጠን ይሰፋል ተብሎ በሚታሰበው የአገሪቷ ድንበር አካባቢ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት የኮሮና መከላከያ ሙሉ ልብስ እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

በዚህም በአማራ ክልል መተማ ያለውን ሰፋ ያለ እንቀሰቃሴ ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም ሱማሌና አፋር ክልሎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በመኖሩ ለእያንዳንዳቸው 15 የፕላስቲክ አልባሳት ይሰጣል ብለዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በሃላፊነት ስሜት ለጸጥታ ኃይሎች እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።

የፖሊስ አባላት ከመንግስትና ከሕዝብ የሚሰጡ ሃላፊነቶችን በብቃት ለመወጣትና ከወረርሽኙ በአጭር ጊዜ ለመውጣት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

ድጋፉን ከክልሎች፣ ከፌዴራልና ከከተማ አስተዳደር የተገኙ ተወካዮች ከሚኒስትሯ ተረክበዋል።

የሠላም ሚኒስቴር የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥልና የችግሩ አሳሳቢነት በሚበዛባቸው አካባቢዎች ትኩረት እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም