ሰላማችንን በማስጠበቅ ለአገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ቀጣይት እንሰራለን- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነዋሪዎች

71
አሶሳ ሰኔ 29/2010 የክልሉን ሰላም በመጠበቅ በአገሪቱ ለተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ቀጣይነት የድርሻቸውን ለማበርከት እንደሚሰሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነዋሪዎች ተናገሩ። በክልሉ በተወሰኑ ወረዳዎች ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በክልሉ ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን የማይወክል ድርጊት በመሆኑ እንደሚያወግዙትና አብሮነታቸውን በማጠናከር ሰላማቸውን እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡ ከክልሉ ሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከክልሉና ከፌደራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ትናንት  በአሶሳ ከተማ መክረዋል። በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የአሶሳ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዱልመሃሙድ ኢብራሂም በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ያነሳሱት በአገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚፈልጉ አካላት መሆናቸውን ተናግረዋል። በማህበረሰቡ ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሙ በመመካከር የመፍታት ልምድ እንዳለ በማስታወስ የተፈጠረው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ይህን ልምድ አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት። በተከሰተው የፀጥታ ችግር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ የክልሉ ፖሊስ አባላት  መኖራቸውን አስታውሰው፣ መንግስት እነዚህን አጥፊዎች እንዲጠየቅና የአቅም ችግር ያለባቸውም ተጨማሪ ስልጠና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። “የክልሉ ነዋሪዎች ወደ መሀል አገር በምናደርገው እንቅስቃሴ በአጎራባች ክልል ወረዳዎች ችግር እየገጠመን በመሆኑ የፌደራሉና የክልሉ መንግስት መፍትሄ ይስጠን” ብለዋል ። “በህዝቦች መካከል ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የሰው ሕይወት እንዲጠፋ የሚፈልጉ አካላት የማንንም ብሔር አይወክሉም” ያሉት ደግሞ አቶ ከበደ አደራ የተባሉ የማንዱራ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በወረዳቸው በተካሄደ ህዝባዊ ውይይት ሁከትና ብጥብጥ ሊያስነሱ የሚፈልጉ አካላት መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ህዝቡ ለሠላሙ ባለው ቁርጠኝነት ትጥቁን በመፍታት ለአካባቢው ሠላም መረጋገጥ ያለውን ጽኑ ፍላጎት አረጋግጧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው የሰፈነውን ሰላም አጠናክሮ በማስቀጠልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመደገፍ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም አመልክተዋል። የአሶሳ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዱራሂም ዑመር በበኩላቸው በክልሉ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟቸውን ችግሮች በጋራ እየፈቱ መኖራቸውን አመልክተዋል። ከቀናት በፊት በአሶሳና በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የተፈጠረው ችግር ህዝቡን ሊለያይ እንደማይችልና የህዝብን ሰላምና አንድነት በማይፈልጉ ኃይሎች አነሳሽነት የተፈጸመ በመሆኑ አጥብቀው እንደሚያወግዙት ተናግረዋል። በክልሉ መንግስት ተቋማት ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት አለመሰጠቱ ለችግሩ የራሱ አስተዋጽኦ ስላለው በቀጣይ የአመራሩ የህዝብ አገልጋይነት ትኩረት ተሰጥቶ እንዲፈተሽ ጠይቀዋል። የፓዌ ወረዳ ነዋሪ አቶ አለማየሁ ባሶሬ በበኩላቸው የተፈጠረው ችግር ጥቅማቸውን ያጡ አካላት የሚያነሳሱት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በክልሉ እስከ ታችኛው መዋቅር ያሉ አመራሮችን በመፈተሽ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባል ያሉት አቶ አለማየሁ፣ በቀጣይ አንዱን ብሔር ከሌላው ለማጋጨትና እየታየ ያለውን የለውጥ ጅማሮ ለመቀልበስ የሚጥሩ ጥቅመኞችን ለመከላከል ሌት ተቀን እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በክልሉ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ አንድነትን ለማጠናከር የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በማይደግፉ ኃይሎች ጠንሳሽነት የተፈጸመ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በሚኖሩ የተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል ያለውን አብሮ የመኖር ባህል በማጠናከርና  አንድነትን በማጎልበት  የክልሉንም ሆነ የህዝቡን ሰላም መጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። ለዚህም ህብረተሰቡ በየአካባቢው ሰላሙን ለማስጠበቅ የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ በማስቀጠል ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ በክልሉ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ልዩነትን ከሚያሰፉ ሃሳቦች ይልቅ የቀደመ አንድነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ወደ መሀል አገር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች መጉላላት እየደረሰብን ነው በሚል የተነሳውን ቅሬታ ለመፍታት የፌደራሉ መንግስት ከክልሉ መንግስት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ መንግስትም በፀጥታ አካላትና በአመራሮች ላይ የጀመረውን የማጥራትና ተጠያቂዎችን ወደፍርድ የማቅረብ ሥራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅም ህዝቡ ለፀጥታ ስጋት የሚሆን ለየት ያሉ እንቅስቃሴዎችን ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር መከታተልና ለሚመለከተው የመንግስት አካል ፈጥኖ እንዲያሳውቅ  አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም