በመዘናጋት ጉዳት ላለማስተናገድ...

49

አብዱራህማን ናስር(ኢዜአ)

“በሀገራችን ጣሊያን እጅግ አሳዛኝ ነገር እየሆነ ነው። በእድሜያቸው የገፉ ሕሙማን ከመሞታቸው በፊት በጉንጮቻቸው ላይ እንባቸው ሲወርድ ይታያል። ከቀረባቸው አደጋ ሊያመልጡ የሚችሉበት ምንም ዕድል የላቸውም። ሁሉም ጭንቀታቸውን እንደተሸከሙ ነው እያንቀላፉ ያሉት። አብዛኛውን ጊዜ ባልና ሚስት በአንድ ቀን ይሞታሉ። ቅድመ አያቶችና አያቶች፤ በመጨረሻዋ ሰአት የልጅ ልጆቻቸውን መሰናበት አልቻሉም።አሁን እኛ ዶክተሮቹ እያለቀስን ነው። ነርሶቻችንም እያነቡ ነው። የሀዘናችን ምክንያት የብዙ ሰዎችን ህይወት መታደግ አለመቻላችን ነው ”ጣሊያናዊው ዶክተር ዳኒየሌ ማቺኒ በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጪ በመውጣቱ ያስከተለው ቀውስ በየእለቱ ሺዎችን መቅጠፍ በጀመረበት ወቅት የተናገሩት ነበር።

በጣሊያን የቫይረሱ ስርጭት ከመስፋፋቱ በፊት በየካቲት 2012 አጋማሽ በሮም ሁለት የቻይና ቱሪስቶች በቫይረሱ ስለመያዛቸው ተነግሮ ነበር። በወቅቱ ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎች እንዲሰረዙ ከመደረጉ ውጪ የተለየ እርምጃ አልተወሰደም።

በቻይና ታህሳስ ወር ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ቻይናን አዳርሶ ወደ ሌላው የዓለም አገራት ለመስፋፋት የፈጀበት ጊዜ ከአንድ ወር አይበልጥም። በየካቲት ወር መጀመሪያ ሳምንት በጀርመን፣ ጃፓንና ቬትናም 8 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

ወረርሽኙ በፍጥነት እንደሚሰራጭና እጅግ ፈታኝ እንደሚሆን የተገነዘበው የዓለም የጤና ድርጅት በሽታው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን ጥር ወር አጋማሽ ቢያውጅም ጣልያንና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገሮች ከቁብ አልቆጠሩትም። ቻይና ሁሉንም እንቅስቃሴ ዘግታ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ደፋ ቀና ስትል እየተመለከቱ አብዛኛዎቹ አገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው በየቀኑ እንደቅጠል በሻይረሱ ሳቢያ መርገፍ ጀምረው መያዣ መጨበጫ እስኪያጡ ድረስ ከተለመደው የተለወጠ እርምጃ አልወሰዱም ነበር።

በወረርሽኙ ያልተፈተነ አገር ባይኖርም እንደ አሜሪካ፣ ጣሊያን እና ስፔን የመሳሰሉ አገራት ክፉኛ ተጎድተዋል። እነዚህ አገራት ለከፍተኛ ቀውስ የተዳረጉት ወረርሽኙ በአገራቸው መከሰቱን ተከትሎ መሪዎቹም ይሁን ህብረተሰቡ ቸልተኝነትና መዘናጋት በማሳየታቸው ነው። በአንፃሩ እንደ ቻይና፣ ታይዋን፣ ጀርመን እና ደቡብ ኮሪያ ገና ከጅምሩ በወሰዱት ጥብቅ ቁጥጥር ለከፋ ጉዳት ሳይዳረጉ ሊቆጣጠሩት ችለዋል።

ጣሊያናውያን በማህበራዊ አኗኗራቸው ከምእራባውያን ይለያሉ። ትስስራቸውና ቅርርባቸው ጥብቅ ከመሆኑም ባሻገር የቤተሰብ አባላት ያላቸው መከባበርና መደጋገፍ እንዲሁም አብሮ መብላትና በጋራ የመዝናናት ልምዳቸው ጠንካራ እንደሆነ ይነገርላቸዋል። የኮሮና ቫይረስ በጣሊያን መሰራጨት እንደጀመረ ቫይረሱ ጣሊያናውያንን የማይነካ እስኪመስል ድረስ ሕዝቡ በየቦታው መሰባሰቡ፣ መዝናናቱ እና ሌሎች ተግባራት ሁሉ እንደወትሮው ቀጥለው ነበር። ከለመዱት የአኗኗር ዘዬ በቀላሉ ሊላቀቁ አልቻሉም።

በሀገረ ጣሊያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉም ነገር ድንገት ተቀየረ። ወረርሽኙ ተስፋፍቶ ብዙዎችን አልጋ ላይ አስቀረ። ሆስፒታሎች ቦታ ጠበባቸው፤ የህክምና ባለሙያዎች አቅም አጠራቸው። በየሰዓቱ ለህክምና ወደ ተለዩ ቦታዎች የሚፈሰው ቁጥር እየጨመረ መጣ። በየእለቱ ከበሽታው ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ስለነበር ሁኔታውን የሚዘግቡ የመገናኛ ብዙሃን በረከቱ፤ የዓለም ሁሉ ትኩረት ጣሊያን ሆነች።

በዚህ ሁኔታ የተደናገጠው የጣሊያን መንግስት በመጋቢት ወር መጀመሪያ ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ አገሪቱ በማወጅ ህዝቡ በር ዘግቶ እንዲቀመጥ ጥብቅ መመሪያ አስተላለፈ። ሆኖም እርምጃው “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንደሚባለው ሆነና የበሽታው ስርጭት ከቁጥጥር ውጪ ሆነ፤ የዳበረው ኢኮኖሚያቸው እና የዘመነው የጤና መሰረተ ልማታቸው ሊቋቋመው አልቻለም።

በየቀኑ የሚረግፉ ዜጎቻቸው ቁጥር ለመናገር የሚያዳግት ሆነ። በዚህ ወቅት ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ተስፋ የቆረጠ በሚመስል አንደበት  “በምድር ላይ ያለውን ሁሉ ሞክረን አልተሳካልንም፤ የቀረን ወደ ፈጣሪ ማንጋጠጥ ብቻ ነው” ሲሉ እምባ እየተናነቃቸው የተናገሩት። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ የተጠቃችው ጣሊያን በአራት ወራት ውስጥ ከሁለት መቶ ሰላሳ አንድ ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ከሰላሳ ሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸውን አጥተዋል።

በጥር ወር አጋማሽ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ስለመገኘታቸው ባሳወቀችው አሜሪካም ቫይረሱ ውስጥ ለውስጥ ይዛመት የነበረ ቢሆንም እንቅስቃሴዎች ላይ የተጣለ ገደብ አልነበረም። እስከ የካቲት ወር መጀመሪያ ሳምንት ህይወት እንደወትሮው ቀጥሏል፤ ትምህርት ቤቶች፣ የአምልኮ ስፍራዎች፣ የባህር ዳርቻ መዝናኛዎች፣ የምሽት ክለቦች ሁሉም ክፍት ነበሩ። በመንግስት በኩል የነበረው መዘናጋትም ከፍተኛ እንደነበር ብዙዎች ይተቻሉ።  በአጭር ጊዜ እንደሚቆጣጠሩትም በተደጋጋሚ ሲገልጹ ነበር። በወሩ መገባደጃ ግን ሁኔታዎች መቀያየር ጀመሩ።

በመጋቢት ወር መጀመሪያ በአሜሪካ በ16 ግዛቶች ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 150 እንደደረሰ በወቅቱ የተለያዩ ሚዲያዎች አስነብበዋል። በዚሁ ወቅት በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አስራ አንድ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸው አለፈ። የህክምና ባለሙያዎች ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ቢያስጠነቀቁም በብዙ ቦታዎች የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚገድቡ እርምጃዎች አልተወሰዱም። በጆርጂያ፣ ኦክልሀማና አላስካ ግዛቶች የንግድ ቦታዎች ክፍት ነበሩ። በፍሎሪዳና ካሊፎርንያ ግዛቶችም ሰዎች እንደተለመደው ለመዝናናት ወደ ባህር ዳርቻዎች ሲያቀኑ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በነበረችው አሜሪካ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ55 ሺ በላይ ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ800 በላይ ደረሰ።

ይህም ሆኖ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በትንሽ ጊዜ የሚጠፋ ቀላል ጉንፋን ነው፣ እኛን አያሳስበንም” በማለት አጣጥለውታል። ቀጥሎም አሜሪካ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከኮሮና ነጻ ትሆናለች ሲሉ በመገናኛ ብዙሀን ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ይህን የተናገሩት የዓለም የጤና ድርጅት አሜሪካ ቀጣይዋ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕከል እንደምትሆን ስጋቱን መግለጹን ተከትሎ ነው።  ፕሬዚዳንቱ እንደገመቱት ቫይረሱ በአጭር ጊዜ የሚጠፋ መሆኑ ቀርቶ በፍጥነት በመሰራጨት አገሪቱን አንበረከከ። በዚህ ወቅት ነበር በቫይረሱ ስርጭት ክፉኛ የተጎዳችው የኒዮርኩ ገዢ "ወረርሽኙ እንደ ፈጣን ባቡር በፍጥነት እየተምዘገዘገ ነው" ሲሉ የገለጹት።

አሜሪካ በሂደት የዜጎቿን እንቅስቃሴ ለመገደብ ብትገደድም የቫይረሱ ስርጭት በፍጥነት በመስፋፋቱ ለመናገር በሚያዳግት ደረጃ ለጉዳት ተዳርጋለች። አገሪቱ ቫይረሱ በተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን በሟቾች ብዛት ከዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ተቀመጠች። በአንድ ቀን ብቻ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የሚያዙባት እንዲሁም ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸውን የሚያጡባት አገር ለመሆን በቃች። 

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አሜሪካ በኮሮና ቫይረስ የሞቱባት ዜጎች ቁጥር ባለፉት 44 ዓመታት በቬይትናም፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታንና በኮሪያ ጦርነቶች የሞቱባት ዜጎች ተደምረው እንኳ አልደረሰበትም። በጆን ሆፕ ኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ መሰረት በሀገሪቱ እስከ ግንቦት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ቁጥር ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ106 ሺህ በልጧል። ይህም በዓለም በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች 30 በመቶውን ድርሻ ይይዛል።

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ  ሰው መገኘቱ ከታወቀ ከሁለት ወራት በላይ አስቆጥሯል። መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በኮሮና ቫይረስ የተያዘ አንድ ጃፓናዊ መገኘቱን በጤና ሚኒስቴር ሲገለጽ በህብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረው ድንጋጤ ከፍተኛ ነበር። በሶስተኛው ሳምንት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉ ሲነገር ደግሞ ድንጋጤው እንዲባባስ አደረገው። መንግስትም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ርብርብ ማድረግ ጀመረ። በወቅቱ  በህብረተሰቡ ዘንድ ሌሎች አገሮች የተፈተኑበት ይህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ አገራችን ከገባ እልቂት ይፈጠራል የሚል ከፍተኛ ስጋት ነበር።

ቫይረሱ በአገራችን መከሰቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) መጋቢት 7 ቀን 2012 የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ይረዳል የተባሉ መመሪያዎችን አስተላልፈዋል። በዚህም  ትላልቅ ሕዝባዊ ስብሰባዎች መከልከላቸው፣ አነስተኛ ስብሰባዎችም ቢሆኑ ያለ ጤና ሚኒስቴር እውቅና እንዳይካሄዱ፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም በስተቀር ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ የኃይማኖት ተቋማት ለአምልኮ የሚታደመውን ሰው ቁጥር እንዲቀንሱ ተደረገ። ከትንሽ ጊዜ በኋላም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ማናቸውም መንገደኞች በተመረጡ ሆቴሎች ለአስራ አራት ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቀመጡ ተወሰነ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሰላሳ አገራት የሚያደርገውን በረራ እንዲያቆም ተደረገ። በመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት በኩል ስለቫይረሱ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ስራዎች በስፋት መስተናገድ ጀመሩ።

እነዚህ እርምጃዎች አዎንታዊ ሚና የነበራቸው ቢሆንም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥርና አድማስ ቀስ በቀስ እየጨመረ መጥቷል። በመጋቢት ወር 55 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ የሁለት ሰዎች ህይወት ደግሞ አልፏል። በዚህ ምክንያት መንግስት ቀደም ሲል ያስተላለፋቸው ውሳኔዎችን ለማጠናከርና ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተገደደ። በዚህም የተነሳ መጋቢት 30 ቀን 2012 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ። የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የአዋጁ መውጣት እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑ በሚከተለው ሃሳብ ተብራርቷል።   

“መንግሥት ችግሩን በደረሰበት ልክ ለመቋቋም ተዘጋጅቷል። የምንወስዳቸው ውሳኔዎች ክብደት እንደ ችግሩ ክብደት የሚወሰን ነው፡፡ ታሪክ እዚህ አድርሶናል፡፡ ሀገርና ትውልድ በእጃችን ላይ ነው፡፡ በዚህ ዘመን በምንሠራው ሥራ ወይ እንመሰገናለን ወይ እንወቀሳለን፡፡ ከምንም በላይ ግን በጊዜውና በዐቅማችን ማድረግ ያለብንን ካላደረግን የበለጠ እንወቀሳለን፡፡ ይህ ደግሞ ሁላችንንም ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት ነው፡፡ ከተረፍን አብረን ነው፡፡ ከከሠርንም አብረን ነው፡፡”

በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ የውጪ አገራት የጉዞ ታሪክ ያላቸው ወይም በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ቀጥታ ንክክኪ የነበራቸው ናቸው። ይህም ብቻ ሳይሆን በየእለቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ10 በታች ነበር። የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል። ይህ ሁኔታ ቫይረሱ ወደ ህብረተቡ አልገባም በሚል በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት የፈጠረ ይመስላል። በተለይ በፋሲካ በዓል ሰሞን በአዲስ አበባ የግብይት ማእከላት የነበረው መተፋፈግ ማሳያ ነው። በትራንስፖርት ቦታዎች የሚታየው ግፊያም ምን ያህል መዘናጋት እንዳለ አመላካች ነው። በካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች እና በሌሎች የቢዝነስ ተቋማት አካባቢም እንቅስቃሴዎች በተለመደው መልኩ ሲከናወኑ ተስተውሏል።

ከሚያዝያ ወር የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ ሁኔታዎች መቀየር ጀመሩ። በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት ጭማሪ አሳየ። በመጋቢትና ሚያዝያ  ወራት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 194 የነበረ ሲሆን በግንቦት ወር በሃያ ቀናት ውስጥ ብቻ 869 ሰዎች በበሽታው ተይዘው አጠቃላይ ቁጥሩ ከአንድ ሺህ በልጧል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 717 ሰዎች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። የቫይረሱ ስርጭት ባለፉት ሁለት ወራት ከነበረው በአራት እጥፍ ጨምሯል። በጤና ሚኒስቴር ሪፖርት መሰረት በግንቦት ወር ውስጥ በአንድ ቀን ብቻ 137 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የቫይረሱ ስርጭት በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች መዛመቱ ከህብረተሰቡ የአኗኗር ሁኔታ ጋር በተያያዘ ችግሩ ይበልጥ እንዲወሳሰብ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። አብዛኛዎቹ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች የውጪ ጉዞ ታሪክ ወይም በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቀጥታ ግንኙነት የሌላቸው ናቸው። ይህም እያንዳንዱ የከተማው ነዋሪ በቫይረሱ የመያዝ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን አመላካች ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ እንደገለጸው ከሆነ በከተማው አሁን ከተደረሰበት ተጨማሪ ምርመራ ቢደረግ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሻቅብ ይችላል። 

በአዲስ አበባ ከተማ የቫይረሱ ስርጭት በሁሉም ክፍለ ከተሞች መገኘቱ ወረርሽኙ በማኅበረሰቡ ውስጥ ገብቶ እየተሰራጨ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ባለሙያዎቹ እንደሚገልጹት አንድ ወረርሽኝ ማህበረሰቡ ውስጥ ገብቷል ሲባል በቫይረሱ የሚያዘው ሰው በሽታው የተላለፈበት በዙሪያው ካለ ሰው ሲሆን ነው። ወረርሽኙ በዚህ ደረጃ ላይ ከደረሰ ደግሞ ወደ ጎን በቀላሉ የመስፋፋት ዕድሉ ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር ፍጥነቱም ይጨምራል ሲሉ ይገልጻሉ። ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በምርመራ እስኪታወቁ ድረስ በርካታ ንክኪ ስለሚኖራቸው በሽታውን በቀላሉ የማሰራጨት እድል አላቸው። ይህ ደግሞ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሚሆን ያስረዳሉ።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ስነልቦናዊ ቀውስን አስከትሏል። ወረርሽኙ አሜሪካንና ጣሊያንን የመሰሉ የዳበረ ኢኮኖሚ ያላቸው አገራትን አንበርክኳል። ተመራማሪዎች በየአቅጣጫው ከፍተኛ ምርምር ቢያደርጉም እስካሁን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችል መፍትሔ አልተገኘም። ይልቁንም ስርጭቱ በፍጥነት እየጨመረ አሁን ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ6 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

በአገራችንም እስካሁን ባለው መረጃ ስርጭቱ ከጋምቤላ ክልል በስተቀር  በቫይረሱ የሚያዙ ወገኖች ቁጥር እጅግ በፍጥነት እየጨመረ መጥቷል። ስርጭቱ በዚህ ከቀጠለና በህብረተሰቡ ዘንድ እየታየ ያለው መዘናጋት ካልታረመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቁጥጥር ውጪ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። የብዙ አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየውም ይህንኑ  በመሆኑ በመዘናጋት የማንወጣውን ጉዳት ከማስተናገድ ሁሉም የበኩሉን ጥንቃቄ ያድርግ መልዕክታችን ነው። ሰላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም