አየር መንገዱ ወርሃዊ ወጪውን ሸፍኖ ለአገር ኢኮኖሚውም ድጋፍ እያደረገ ነው

81

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ120 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማስገባት ወርሃዊ ወጪውን ሸፍኖ ለአገር ኢኮኖሚ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ዋና ሥራአስፈጻሚው ተናገሩ።

ዋና ሥራአስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት አየር መንገዱ ፈጥኖ ወደ ካርጎ አገልግሎት መግባቱ  ውጤታማ አድርጎታል።

ኮቪድ- 19 በዓለም ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ በአየር መንገዱ ላይም ተመሣሣይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸው፤ በርካታ አየር መንገዶች በድጎማና በብድር ውስጥ በገቡበት ወቅት አየር መንገዱ ወጪውን ሸፍኖ ለመንግሥት ድጋፍ ለማድረግ በቅቷል ብለዋል።

ለውጤታማነቱ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የኮቪድ- 19 መከላከያ ቁሳቁስ የሚተላለፍባት ምቹ ቦታ ተደርጋ መወሰዷና አየር መንገድ በዓለም ገበያ ላይ አበባ ለማጓጓዝ ተመራጭ እንዳደረገው አመልክተዋል።

አየር መንገዱ በቀን ከ200 እስከ 300 ቶን አበባ ወደ ተለያዩ አገሮች በማጓጓዝ በኢትየጵያ ያለውን የአበባ ምርት እንዲበረታታና በውጭ ምንዛሪ ኢኮኖሚውን እየደገፈ ነው ብለዋል።

በረመዳን ወቅት ሥጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በማጓጓዝ ገቢ ማግኘቱን ዋና ሥራአስፈጻሚው አብራርተዋል።

አየር መንገዱ ወጪውን ሸፍኖ ለአገሪቱ ኢኮኖሚው ድጋፍ ማድረጉ በዓለም ካሉት አየር መንገዶች ጠንካራ ያስብለዋል ብለዋል።

በቀጣይም የዓለም አቀፉን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማየት ተጨማሪ የመንገደኛ አውሮፕላኖችን ወደ ጭነት ማመላለሻነት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ተወልደ አስታውቀዋል።

የአየር መንገዱ 90 በመቶ የመንገደኞች አውሮፕላኖች የኮሮና ቫይረስ ባመጣው ተፅዕኖ ምክንያት ሥራ አቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰባት አሥርታት በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል።

ከአፍሪካ ግንባር ቀደም አየር መንገዶች አንዱ እንደሆነም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም