የደወሌ ኬላ ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የውሃና ሎጀስቲክስ እጥረት ገጥሞናል አሉ

60

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/2012 (ኢዜአ) በኢትዮ-ጅቡቲ ጠረፍ የደወሌ ኬላ ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በውሃና ሎጀስቲክስ እጥረት መቸገራቸውን ተናገሩ። መንግስትም ስፍራውን በልዩ ሁኔታ ተመልክቶ በአፋጣኝ ችግሮችን እንዲፈታ ጠይቀዋል።

በሶማሌ ክልል አይሻ ወረዳ በኩል ኢትዮጵያ ከጅቡቲ የምትዋሰንበት የደወሌ ፍተሻ ጣቢያ ከትራንስፖርት ባለስልጣን፣ የኢሚግሬሽን፣ የፌዴራልና መከላከያ አባላት፣ የጤና ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን የኮቪድ- 19 ወረርሸኝን ለመከላከል ላለፉት 4 ወራት በስፍራው ይገኛል።

ባለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ ከድሬዳዋ-ደወሌ-ጅቡቲ የሚወሰድ የፍጥነት መንገድ መከፈቱን ተከትሎ በርካታ የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችም የሚመላለሱበት አንዱ መውጫና መግቢያ በር ነው።

ከዚህም ባለፈ መንገዱ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በየዕለቱ በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ኮብላዮች የሚመላለሱበት በመሆኑም፣ ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ ያለበት እንደሆነ ያስረዳሉ።

በከፍተኛ ጣቢያው የተሽከርካሪዎች ኬሚካል ርጭት፣ የሙቀት መለካትና ወደ አገር ቤት የሚገቡ ዜጎችን ለይቶ የማቆየት ስራዎችን ያከናውናሉ።

ያም ሆኖ ላለፉት ወራት በነበራቸው የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት የሚያግዙ ሁኔታዎች እንዳልተሟሉላቸው፣ ይህም ከስፍራው ከፍተኛ ሙቀት ጋር ተዳምሮ ስጋት ውስጥ እንዳስገባቸው ተናግረዋል።

የጣቢያው የጤና ባለሙያዎች አስተባባሪ አቶ መሃመድ ጉኔና የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የደወሌ አስተባባሪ አቶ ከድር የሱፍ በአካባቢው የውሃ እጥረት ችግር አለመፈታቱን አስረድተዋል።

ሰዎችን ለማዘዋወርም የሎጀስቲክስ ችግር እንዳለባቸው ይናገራሉ።

ከድሬዳዋ-ደዋሌ መስመር 2ኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥና የስፍራው ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሻለቃ ዘሪሁን ተረፈና የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባው ሳጅን ኤርሚያስ ጴጥሮስም ችግሩን ይጋራሉ።

ከዋናው ፍተሻ ጣቢያ ውጭም ወደ አገር ቤት የሚገቡ ዜጎች ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ የፀጥታ አካላት ሰዎቹን በቁጥጥር ስር ቢያውልም ለኮብላዮች ማቆያ ስፍራና አገልግሎት የሚሆን ምቹ ሁኔታ እንደሌለ ገልጸዋል።

ለተርሚናል በተዘጋጀና ምንም አይነት የመኝታ አቅርቦት በሌለው ክፍል እንዲቆዩ መደረጉ፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለምግብ እጦት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

ይህም በጊዜያዊ ለይቶ ማቆያ የተቀመጡ ዜጎች በሌሊት ለመጥፋት እንደሚሞክሩ ይናገራሉ።

ውሃ ባለመቅረቡ ከአካባቢው ካሉ የቻይና ድርጅት በልማና እየተጠቀሙ ስለመሆኑ፣ የመከላከያ ግብዓቶችንም በራሳቸው እየገዙ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

የአይሻ ወረዳ ዋና አስተዳደሪም አቶ ኑር ሃሰን በወረዳው 700 ሰዎችን በለይቶ ማቆያ ኳራንታይን መደረጋቸውን ገልጸው፤ እስካሁን ከወረዳው ውጭ እርዳታ ያደረገ አካል የለም ብለዋል።

በመሆኑም የውህ፣ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አቅርቦት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

ከሰሞኑ ስፍራውን የጎበኙት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ ችግሩ መኖሩን ተመልክተዋል።

ለአስቸኳይ መፍትሄነትም ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር በቦቲ የውሃ አቅርቦት እንዲሟላ ይደረጋል ብለዋል።

በዘላቂነት ግን በስፍራው ከሚገነባው የድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች መቆሚያ ግንባታ ጋር ተያይዞ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም