ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በአግባቡ ባለመተግበራቸው ችግሩ መሻሻል አላሳየም

79
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 በኢትዮጵያ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስበው የተቀረፁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በሚተገበሩበት ወቅት የሚታዩ የአፈፃፀም ችግሮች አሁንም ድረስ እንዳልተፈቱ የሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለፀ። ኢትዮጵያውያን ሴቶች በፖለቲካው ዓለም የሚሳተፉበትን ሁኔታ ለማስፋት የሚደረገው ጥረት የተወሰነ ለውጥ እያሳየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በመንግስት የተለያዩ የስልጣን መዋቅሮች በተለይ በስራ አስፈጻሚነት የኃላፊነት ደረጃ ያላቸው ድርሻ ከ13 በመቶ የዘለለ አይደለም። በምጣኔ ኃብት ረገድም ቢሆን ራሳቸውን ጠቅመው ለሌሎች የስራ እድል የፈጠሩ እንዳሉ ሁሉ አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች በድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለአብነትም በመጀመሪያው የእድገና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በአገሪቱ ከተፈጠረው ከአስር ሚሊዮን በላይ የስራ እድል የሴቶች ድርሻ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብቻ ነበር። የሴቶችና ህጻናት ሚኒስትር ወይዘሮ የአለም ጸጋዬ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረጹ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂዎች እና መርሃ-ግብሮች ትግበራ አሁንም ችግሮች እንዳሉበት ያምናሉ። ሚኒስትሯ በተለይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ-መልልስ እንደተናገሩት፤ ከሴቶች ጋር በተያያዘ የተዘጋጁት የፖሊሲና ሌሎች የልማት እቅዶች  የሴቶችን ሁለንተናዊ ህይወት ለመቀየር የሚያስችሉ ቢሆኑም በተገቢው መንገድ ተግባር ላይ ባለመዋላቸው የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት አልተቻሉም። ከዕቅድ እስከ ትግበራ ድረስ ባለው ሂደት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ መስራት አለመቻሉና ሂደቱን ለመከታተል ጠንካራ ስርዓት አለመዘርጋቱ የአተገባበሩ የችግር መንስዔ እንደሆኑ ጠቁመዋል። በተለይም ደግሞ በግንባታ፣ በማምረቻ፣ በኢንዱስትሪና ሌሎች ዘርፎች የሴቶች ተሳትፎ ውስን መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ በሚቀጥሉት ዓመታት ለውጥ ለማምጣት ከሚመለከታቸው ጋር ለመስራት የሚያስችል አሰራር እንደሚዘረጋ ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ወደፊት በዝርዝር የሚገመገም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በእቅዱ ከተወሰዱት እርምጃዎች ጋር በተያያዘ ለውጦች መኖራቸውን አብራርተዋል። ሴቶቸ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያላቸውን 38 በመቶ የተሳትፎ ድርሻ ወደ 50 በመቶ፣ በስራ አስፈጻሚነት ደረጃ ያላቸውን ተሳትፎ ደግሞ ወደ 40 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም