የደንዲ ወረዳ አርሶ አደሮች በቢራ ገብስ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ ነው

59
አምቦ ሰኔ29/2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን የደንዲ ወረዳ አርሶ አደሮች የቢራ ገብስን በኩታ ገጠምና በመስመር በመዝራት ምርታማነትን ለማሰደግ እየሰሩ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን በተያዘው የመኸር እርሻ 4 ሺህ 655 ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ  ዘር የመሸፈን ሥራ ትናንት በደንዲ ወረዳ ተጀምሯል፡፡ በወረዳው የከትከታ ወረን ቡልቺ ቀበሌ አርሶ አደር ተሾመ ዴሬሳ በሰጡት አስተያየት በቢራ ገብስ ልማት መሳተፍ የጀመሩት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ነው። ዓምና በግማሽ ሄክታር ላይ ካለሙት የቢራ ገብስ 15 ኩንታል ምርት በማምረት 22 ሺህ 500 ብር ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። በዘንድሮ የመኸር እርሻ መሳቸውን በኩታ ገጠምና በመስመር በመዝራት ከዓምናው የተሻለ ምርት ለማግኘት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሌላው የቀበሌው ነዋሪ  አርሶ አደር በዳቱ ለቺሳ በበኩላቸው "ተመሳሳይ ሰብልን በኩታገጠም ማልማት ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ወጥ በሆነ መንገድ ለመጠቀምና ማሳን በጋራ ለመንከባከብ  ምቹ  ሁኔታ ፈጥሮልናል" ብለዋል። ቀደም ሲል በሩብ ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ በመዝራት ያገኙት የነበረው ምርት ከአራት ኩንታል ይበልጥ እንዳልነበር ጠቁመው፣ ባለፈው ዓመት በኩታ ገጠም ከዘሩት የቢራ ገብስ ያገኙት ምርት በአጥፍ ማደጉን ተናግረዋል። ይህን እንደመልካም ተሞክሮ በመውሰድ በዘንድሮው የምርት ዘመን  በግማሽ ሄክታር  ማሳቸው ላይ በኩታገጠም የቢራ ገብስ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል። የቀባ በሬዳ ቀበሌ አርሶ አደር በቀለ ኡማ በበኩላቸው በቀዳሚው ዓመት በባህላዊ አስተራረስ ዘዴ ከግማሽ ሄክታር መሬት አምስት ኩንታል ገብስ ገብስ ማምረታቸውን አስታውሰዋል። በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤና ከሌሎች አርሶ አደሮች በቀሰሙት ልምድ በኩታ ገጠም ተደራጅተው አንድ ሄክታር መሬታቸውን በዘር በመሸፈን እስከ 30 ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል  ኃላፊ አቶ በቀለ ነገዎ በበኩላቸው እንዳሉት የቢራ ገብስ ልማቱን በደንዲ ፣ ጅባት፣  ጀልዱ፣ ድሬ፣  እንጪኒና አምቦ  ወረዳዎች ለማስፋፋት እየተሰራ ነው። በተያዘው የመኸር እርሻ በኩታ ገጠምና በመስመር የአስተራረስ ዘዴ በዞኑ 4 ሺህ 655 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ143 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ተግባራዊ ሥራ ውስጥ መገባቱን ገልጸዋል። ዘንድሮ ምርታማነትን ለማሳደግ ግብ መያዙን የጠቆሙት ኃላፊው በልማቱ ከ19 ሺህ በላይ የተመረጡና ተገቢ ሙያዊ ስልጠና የወሰዱ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት። የቢራ ገብሱ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲመረት የልማት ጣቢያ ሠራተኞች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ በቀለ፣ ምርቱን የአሰላ ብቅል ፋብሪካ በተመጣጣኝ ዋጋ ስለሚረከብ አርሶ አደሩ የገበያ ችግር እንደማይገጥመው ገልጸዋል። በዞኑ ዓምና ከተካሄደው የቢራ ገብስ ልማት 139 ሺህ  ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለማግኘት ማቸሉ ታውቋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም