የራያ ቆቦ ወረዳ ሁለት ከፍተኛ አመራሮች በተፈጸመባቸው ጥቃት ህይወታቸው አለፈ

157

ባህርዳር (ኢዜአ) 23/2012 የራያ ቆቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና የወረዳው የሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት በተፈጸመባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉን የሰሜን ወሎ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አሳዬ ተገኘ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለቱ የስራ ኃላፊዎች ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በወረዳው 08 ቀበሌ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከለከለውን ሰርግ ለማድረግ የተዘጋጁ ሰዎችን ድርጊት ለማስቆም ከደጋሾቹ ጋር ተነጋግረው ሲመለሱ ነው።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስዩም መስፍንና የወረዳው የሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንገሻ ሞላ በመንገድ ላይ ሳሉ የሰርጉ ታዳሚዎች በአንድ ባጃጅ በብዛት መሳፈራቸውን በማየታቸው አሽከርካሪውን አስቁመው ሲያናግሩ ከተሳፋሪዎች በተተኮሰ ጥይት የሁለቱም ህይወት ማለፉን አስረድተዋል።

ዛሬ ከቀትር በኋላ ከራያ ቆቦ ወረዳ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ 08 ቀበሌ ልዩ ስሙ አራዶ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ላይ ወንጀሉን የፈጸሙት ተጠርጣሪዎችም ታርጋ በሌለው ሌላ ባጃጅ ተሳፍረው ከአካባቢው መሰወራቸውን ተናግረዋል።

የዞኑ እና የወረዳው የጸጥታ ኃይሎችም በጋራ በመሆን የወንጀሉን ፈጻሚዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ ለማቅረብ የተጠናከረ የክትትልና የአሰሳ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም