በዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን እየተከበረ ነው

393

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) በዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን ዛሬ በዓለም ለ33ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።


ቀኑ በየዓመቱ ግንቦት 23 ቀን የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም በዓለም “ወጣቶችን ከኢንዱስትሪ ተፅዕኖ በመከላከል፤ ከትምባሆ እና ኒኮቲን መጠቀም እንጠብቃቸው!” በኢትዮጵያ ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ “የትምባሆ ምርቶችን ባለመጠቀም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ጉዳት እንከላከል!” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።


የዓለም የጤና ድርጅት ቀኑን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ በዓለም በየዓመቱ በቀጥተኛ መልኩ ከትምባሆ ጋር በተያያዘ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሚሞቱና 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ለትምባሆ ጭስ በመጋለጣቸው ለሞት እንደሚዳረጉ አስታውቋል።

በዓለማችን ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ያሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት መካከለኛ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚገኙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ከሶስት ዓመት በፊት በጋራ የሠሩት የዳሰሳ ጥናት በኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ትምባሆ አጫሾች እንዳሉ ገልጸው ነበር።

ከነዚህም መካከል በጎልማሳነት የዕድሜ ክልል ከሚገኘው አንድ ሦስተኛ ያህሉ ደግሞ በሌሎች በሚጨስ ትምባሆ ለተዘዋዋሪ አጫሽነት መጋለጡን ያሳያል።

ለተዘዋዋሪ አጫሽነት ከተጋለጠው ኅብረተሰብ መካከል በቡና ቤቶችና በምሽት ክበቦች፣ በሬስቶራንቶችና በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ አብዛኛውን ድርሻ እንደሚይዙ የዳሰሳው ጥናት ያመለክታል።

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ ''የኮቪድ-19 ቫይረስ በንኪኪ እና ከትንፋሽ ጋር በሚወጣ ነጠብጣብ የሚተላለፍ በመሆኑ ሲጋራና ሺሻ እየተቀባበሉ በሚያጨሱ ሰዎች መካከል በቀላሉ ይተላለፋል'' ብሏል።

ትምባሆ የሚጠቀም ሰው ከማይጠቀም ሰው አንጻር ለከፋ የጤና እክል እንደሚጋለጥም አስታውቋል።

በባህሪው ሁሉንም የሰውነት አካል የሚጎዳው ትንባሆ የኮቪድ-19 በሽታ ሲጨመርበት ለአስከፊ የጤና ጉዳት እንደሚያጋልጥም ነው ባለስልጣኑ የገለጸው።

ስለሆነም ወጣቱ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ከሚፈጥረው ተጽዕኖ ራሱን በመጠበቅና የትምባሆን ገዳይነት በመረዳት ከትምባሆና ኒኮቲን ራሱን መከላከል እንደሚገባውም አመልክቷል።

ህብረተሰቡ ሰዎች ወደ ትምባሆ ምርት ተጠቃሚነት እንዲገቡ የተለያዩ የማማለያ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ አካላትን እንዲከላከልም ባለስልጣኑ ጥሪ አቅርቧል።

በትምባሆ ውስጥ የሚገኘው አነቃቂ ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገር "ኒኮቲን" ስያሜውን ያገኘው በ16ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሰዎች ትምባሆን መጠቀም በጀመሩበት ወቅት ህመምን ይፈውሳል ብለው ያምኑ እንደነበርና እ.አ.አ. ከ1920ዎቹ በኋላ ግን ትምባሆ ማጨስ የጤና እክሎች ያመጣል ተብሎ መታመን መጀመሩ ይገለጻል።

በዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን የሚከበረው ትምባሆ የሚያደርሳቸውን ጉዳቶችና የትምባሆ ድርጅቶች ያላቸውን የንግድ ተግባራት ላይ ሰዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሆነ የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል።

በዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን ሀሳብ የመጣው እ.አ.አ 1987 በተካሄደው የዓለም የጤና ጉባኤ ሲሆን በጉባኤው ላይ "በዓለም ምንም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን" የሚል የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል።

ጉባኤው በቀኑ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ለ24 ሰአት ትምባሆ ከመጠቀም ራሳቸውን እንዲቆጥቡ የሚል የውሳኔ አቅርቦ በቀጣዩ ዓመት ጉባኤ ውሳኔው ጸድቆ የዓለም ትንባሆ የማይጨስበት ቀን በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም