በጎንደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮና ህሙማን በመከታተል ላይ ያሉ ሀኪሞች የህዝብ ድጋፍ ጠየቁ

61

ጎንደር፣ ግንቦት 23/2012 ( ኢዜአ) በጎንደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮና ህሙማን በመከታተል ላይ ያሉ ሀኪሞች ህብረተሰቡ እራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ እንዲያግዛቸው ጠየቁ ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር በሪሁን ካሳው በሆስፒታሉ ለኮሮና ታማሚዎች የህክምና ድጋፍ የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎችን ትናንት በአካል በመገኘት አበረታተዋል፡፡

በሆስፒታሉ የኮሮና ህክምና መስጫ ማእከል ተመድባ የምትሰራው ሲስተር ሀረገወይን ፀሐይ እንዳለችው ህዝቡ አሁን ላይ ከምን ጊዜውም በላይ ከመዘናጋት ወጥቶ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሊተገብር ይገባል ።

"ህዝቡ ተገቢው ጥንቃቄ ካላደረገ በስተቀር እየተስተዋለ ያለው መዘናጋት ዋጋ የሚያስከፍልበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም" ያለችው ሲስተር ሀረገወይን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገጉ ክልከላዎችን በጥብቅ ዲስፕሊን መፈፀምና ማስፈጸም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ፡፡

"የኢቦላ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ላይቤሪያ ድረስ በመሄድ ለስድስት ወራት ግዳጄን ፈጽሜ መጥቻለሁ። ዛሬ ደግሞ የኮሮና በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ግንባር ቀደም ሆኘ ወገኔን እያገለገልሉ እገኛለሁ"  ያለችው ሲስተር ሀረገወይን ህዝቡም እራሱን በመጠበቅ የጤና ባለሙያዎችን እንዲያግዝ ጠይቃለች ።

የጤና ባለሙያዎች ለህይወታቸው ሳይሳሱ ህዝቡን ለመታደግ ከቤተሰባቸው ተለይተው ሌት ተቀን እየሰሩ ነው" በመሆኑም ህዝቡ የበሽታውን አስከፊነት ተገንዝቦ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ምክር ለግሳለች ።

ሌላው በማእከሉ ለኮሮና ታማሚዎች የህክምና ድጋፍ እየሰጡ የሚገኙት ዶክተር አስመቸ መስፍን በበኩላቸው የህዝቡ መዘናጋት በሀኪሞችና በሀገሪቱ የጤና ስርአት ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይደለም።

በማእከሉ ተመድበን የምንሰራው የጤና ባለሙያዎች ዜጎቻችን ከማገልገል ወደ ኋላ ያልንበት ጊዜ ባለመኖሩ በሽታው ወደ ወረርሽኝ ተሸጋግሮ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ህዝቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ከወዲሁ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

"ህብረተሰቡ የበሽታው ተጋላጭ እንዳይሆን ቤት ውስጥ በመቀመጥና ህዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ከመሄድ በመቆጠብ የጤና አገልግሎቱን መደገፍ አለበት" ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር በሪሁን ካሳው በበኩላቸው የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ከሞት ጋር በመጋፈጥ ህዝባቸውን ለማገለግል እያደረጉት ላለው ርብርብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

መስተካከል ይገባቸዋል ተብለው በጤና ሙያተኞቹ የቀረቡትን ጉዳዮች የከተማው የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት መፍትሄ እንደሚያስቀምጥ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘባቸው እንደገለፁት በህክምና ማእከሉ ለአምስት የኮሮና ታማሚዎች አንድ ሀኪም በመመደብ ተገቢውን አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።

የሀኪሞችን የስራ ጫና ለመቀነስና በህክምና ስራ ላይ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ቫይረሱ በምርመራ የተረጋገጠባቸውና ገና ምልክት ብቻ የታየባቸው ታማሚዎች በተለያዩ ሀኪሞች የሚታዩበት አሰራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል፡፡

የህክምና ባለሙያዎቹን ለማበረታታት በተካሄደው የጉብኝትና የምስጋና ፕሮግራም ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም