አዲስ አበባ የክፍያ መንገዶች ይገነቡላታል ... ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ

101

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2012( ኢዜአ) አዲስ አበባ ዋና ከተማነቷን በሚመጥን መልኩ በቀጣይ ከሚገነቡ ትላልቅና ሰፋፊ መንገዶች በተጨማሪ የክፍያ መንገዶች ግንባታ እንደሚጀመር የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ 361 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸውና 6 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ አራት መንገዶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መንገዶቹን አስመርቀዋል።

ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት መንገዶች ከኢትዮ-ፓረንት ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋራዥ፣ ከጅቡቲ ኤምባሲ እስከ ሰሚት ኮንዶሚኒየም፣ ከአራብሳ ኮንዶሚኒየም እስከ አያት ኮንዶሚኒየም እና ከሲኤምሲ-ሰሚት-አያት የሚወስዱ ናቸው።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ከንቲባው እንደተናገሩት፤ የከተማ አስተዳደሩ የአዲስ አበባን ዋና ከተማነት የሚመጥኑ መንገዶች ይገነባሉ።

በዚሁ መሰረት አውራ ጎዳናዎችን ከመገንባት በሻገር አማራጭና መጋቢ መንገዶችን የመገንባት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

''ከተማ አስተዳደሩ በራስ አቅም በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ትላልቅ መንገዶችን መገንባትን በትኩረት ይተገብራል'' ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ከማስተር ፕላኑ ጋር በተናበበ መልኩ በአዲስ አበባ የክፍያ መንገዶች ግንባታ በቅርብ ጊዜ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ሂደቱ አዲስ አበባን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ ወረዳዎችና ከተሞችን አስተሳስሮ ለማሳደግ ያለመ እንደሆነም ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባው እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎችን በመንገድ ከማስተሳሰር በተጨማሪ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች መሰረተ ልማት ለማስተሳሰርም ታቅዷል።

''አዲስ አበባ ዋና ከተማ እንደ መሆኗ ለሌሎች የአገሪቷ ከተሞች አርዓያነት ያለው የልማት ስራዎችን ታከናውናለች'' ብለዋል።

ዛሬ የተጀመሩት መንገዶች ሙሉ ወጪያቸው በከተማ አስተዳደሩ መሸፈኑን  የተናገሩት  የከተማ አስተዳደሩ መንገዶች ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ ናቸው።

ባለስልጣኑ ዛሬ ከተመረቁት መንገዶች በተጨማሪ የከተማዋን የመዲናነት ሚና ሊመጥን የሚችልና ዕድገቷን ሊሸከም የሚችል የመንገድ ግንባታ እየተከናወነ ነው ይላሉ።

መንገዶቹም በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎች ወደ መሓል ከተማ ለሚያደርጉት ጉዞና እርስ በርስ ለመገናኘት አማራጭና አቋራጭ መንገዶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

መንገዶቹ የከተማዋ ነዋሪዎች በትራፊክ መጨናነቅ የሚያባክኑትን ጉልበት፣ ጊዜና ኃብት መቀነስ የሚያስችሉ ናቸውም ብለዋል።

የመንገዶቹ የምርቃ መርሃ ግብር የተካሄደበት የቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየንም አካባቢ ነዋሪዎችና አርሶ አደሮች መንገዱ ከብዙ እንግልት እንደሚያድናቸው ተስፋ አድርገዋል።

ከነዚህ መካከል አቶ አያኑ ጉታ እንደሚሉት፤ መንገዱ ከመሰራቱ በፊት በተለይ በክረምት ወቅት መግባትና መውጣት የማይታሰብ ነው።

''መንገዱ በመሰራቱ ተሽከርካሪዎች በስፋት እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ እናቶች በወሊድ ጊዜ እንዳይቸገሩ ያደረጋል'' ብለዋል።

ሌላው የአካባቢው አርሶ አደር አቶ ድንቁ ደበሌ መንገዱ ''ኑሯችንና ህይወታችን ለከተማ የቀረበ እንዲሆን ያደርጋል'' የሚል ተስፋ ጥለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም መንገዱ የአካባቢው ነዋሪዎች በተለያዩ የልማት አማራጮች ውስጥ እንዲሳተፉ እድልም የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን 100 የሚጠጉ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም