በአዲስ አበባ የኮቪድ-19 ሕሙማንን ለሚያክሙ የጤና ባለሙያዎች ጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶች ተዘጋጁ

58

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2012(ኢዜአ) በአዲስ አበባ የኮቪድ-19 ሕሙማንን እያገለገሉ ለሚገኙ 1 ሺህ 750 የጤና ባለሙያዎች ጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶች መዘጋጀታቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኮቪድ-19ን ለመከላከል ለሚሠሩ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ሠራተኞች የሚውሉ የኢንፌክሽን መከላከያ ቁሳቁስ ለማሟላት እየተሰራ መሆኑንም  የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል።

ዶክተር ሊያ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኮቪድ ሕሙማንን የሚያክሙ የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳያደርጉ በትኩረት እየተሰራ ነው።

የኢንፌክሽን መከላከያ ቁሳቁስ በማቅረብ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንና ጎን ለጎንም ለባለሙያዎቹ ጊዜያዊ መኖሪያ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ ብቻ ለኮቪድ-19 ሕሙማን አገልግሎት ለሚሰጡ 1 ሺህ 750 የጤና ባለሙያዎች የሚያገለግሉ ጊዜያዊ መኖሪያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በሁሉም ክልሎች ጊዜያዊ መኖሪያዎችን ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጤና ባለሙያዎች ባልታወቀ ሁኔታ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሚሆኑበት ሁኔታ ቢፈጠር ተለይተው የሚቆዩበትና በበሽታው ቢያዙ የሚታከሙበት ቦታ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን ተከትሎ ለጤና ባለሙያዎቹ እነዚህ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ መቼና በምን መልኩ ወደ ለይቶ ማቆያ መግባት እንዳለባቸው የሚያመላክቱ መመሪያዎች ከጤና ባለሙያዎችና ከዘርፉ ማኅበራት ጋር በጋራ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች የሚቀርቡ የኢንፌክሽን ቁሳቁስና አልባሳት በግዥ፣ በዕርዳታና በማምረት የማሟላት ሥራም ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

ቁሳቁሶቹን ከውጭ አገር የሚያስመጡ ተቋማት ምዝገባና ተያያዥ ሂደቶችን የማቅለልና አቅርቦቱን የማስፋት ሥራም እንዲሁ።

የኢንፌክሽን ቁሳቁስ ለማምረት በሂደት ላይ ለነበሩ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በፍጥነት ወደ ሥራ ተደርጓል ነው ያሉት ዶክተር ሊያ።

እስካሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ለጤና ባለሙያዎች የሚቀርቡ ደረጃቸውን የጠበቁ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሕክምና የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች /ማስኮች/ መከፋፈላቸውንም አብራርተዋል።

በመጪዎቹ ሣምንታትም በልገሳና በግዥ 25 ሚሊዮን የፊት ጭምብሎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለሕክምና ባለሙያዎች ይሰራጫሉም ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የፊት ጭምብሎች እጥረት መኖሩን የጠቀሱት ዶክተር ሊያ የጤና ባለሙያዎች ይህን ከግምት በማስገባት በጥንቃቄ እንዲጠቀሙባቸውም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም