ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ኮቪድ-19 ን ለመከላከል 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ደገፈ

80

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚያደርገው ጥረት ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ድጋፉ በዋናነት የቀይ መስቀል ማህበር ወረርሽኙን ለመከላከል የሚከናወኑ የቤት ለቤት ፣ ልየታ፣ የጸረ-ተዋህሲያን ርጭትና ለተጋላጭና አቅም ለሌላቸው ወገኖች የመከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ ለማጠናከር ያግዛል። 

የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈፃሚ ሪታ ሮይ ''ይህ ቀውስ ምን ያህል እርስ በርስ የተሳሰርን መሆኑንና ስንተባበር ልዩነት መፍጠር እንደምንችል እያስተማረን ነው'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ፀሀፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ ያደረገው ድጋፍ ማህበሩ እያከናወነ ያለውን የሰብዓዊነትና አደጋ የመቋቋም ተግባራት ጥረቶቻችንን ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

''ወረርሽኙ በማኅበረሰባችን ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመቀነስም በጋራ እንሰራለን'' ብለዋል።

የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ኮንዴ ኮይራ ''ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ችግር ለመፍታት በመጀመሪያ አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው እንደርሳለን'' ብለዋል።

ለጤና ባለሙያዎችና የመጀመሪያ ምላሽ ሰጪዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ የገለጹት ስራ አስኪያጁ ፤ ''ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን ለወጣቶች፣ ጥራት ላለው ትምህርት፣ ለልዩ ክህሎቶች፣ በፋይናንስ አገልግሎቶች እና ለየት ባሉ ስራዎች ላይ ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን'' ሲሉ ገልጸዋል።

ፋውንዴሽኑ ያደረገው ድጋፍ የሰውነት ሙቀት ልኬት ለማካሄድ፣ የኮቪድ-19 ምልክት የሆኑትን እንደ ሳልና መተንፈስ መቸገር ያለባቸውን 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎችን ለመድረስ ታሳቢ ያደረገ የቤት ለቤት ልየታ ሥራ ለማከናወን እንደሚውል ተገልጿል።

በተጨማሪም ድጋፉ ለወረርሽኙ ምላሽ ለመስጠት በግንባር ቀደምትነት በሆስፒታሎችና በለይቶ ማቆያ ማዕከላት ለሚሰሩ 3 ሺህ 800 የጤና ባለሙያዎች መከላከያ አልባሳት፣ ቁሳቁሶችና ንፅህና መጠበቂያዎችን ለማቅረብ እንደሚውል ተገልጿል።

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የእጅ መታጠቢያዎችን በ20 ዋና ዋና ሥፍራዎች የማዘጋጀት ስራዎች እንደሚከናወኑም ማህበሩ በመግለጫው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም