በዲላ ከተማ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ የተጠናከረ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

52

ዲላ /ኢዜአ/ ግንቦት 23 / 2012  በሞያሌ በኩል ከአጎራባች አገሮች የሚገቡ ሰዎች መተላለፊያ በሆነቸው ዲላ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳይስፋፋ የተጠናከረ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የዞኑ የኮሮና መከላከል ግብረኃይል አስታወቀ ፡፡

ግብረኃይሉ እስከ አሁን ድረስም ድንበር አቋርጠው የገቡ 415 ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ  እንዲገቡ አድርጓል ።

የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብረኃይሉ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሳሙኤል ቦኩ ለኢዜአ እንደገለፁት ዲላ ከተማ ከሞያሌና አጎራባች አገሮች የሚገቡ ሰዎች መተላለፊያ በመሆኗ የቫይረሱ ስርጭት ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል ።

ስጋቱን ለመከላከል ደግሞ በሞያሌ በኩል ከኬንያ ድንበሮች በሚገቡ ሰዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል ።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው ለይቶ ማቆያ 14 ቀናትን ያሳለፉ 364 ሰዎች ተገቢውን ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነፃ ሆነው ስለተገኙ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል ።

ቀሪ 51 ሰዎች ደግሞ በለይቶ ማቆያ ማእከሉ በክትትል ላይ መሆናቸውን አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል ።

 በዚህች ከተማ ላይ ተገቢው ቁጥጥር ካልተደረገ የቫይረሱ ስርጭት ለከተማዋም ሆነ ለሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች አስጊ ነው ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው በከተማው የቫይረሱ መመርመሪያ ማእከል እንዲቋቋምላቸው ጠይቀዋል ።

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎቶች ዳይሬክተር አቶ ቢንያም ሽፈራው በበኩላቸው ከጎረቤት አገሮች ወደ ክልሉ ድንበር አቋርጠው ይገቡበታል ተብለው ከተለዩ አካባቢዎች መካከል ዲላ ከተማ አንዷ መሆንዋን ጠቅሰዋል ።

ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ከጠረፍ አካባቢዎች ወደ ከተማው በሚገቡ ሰዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ።

በሀገርም ሆነ በክልል ደረጃ የመመርመር አቅማችንን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ በመሆኑ ለቫይረሱ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የምርመራ ማእከላት ለመክፈት ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም