የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ና ለአቅመ ደካሞች ማዕድ በማጋራት የሸዋል - ኢድ በዓል ተከበረ

52

ሐረር /ኢዜአ/ ግንቦት 22 / 2012 የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የጤና ባለሞያዎችን ምክር በመተግበርና ለአቅመ ደካሞች ማዕድ በማጋራት የሸዋል - ኢድ በዓል ተከበረ፡፡

የክልል መንግስት በአሉን በማይዳሰስ ቅርስነት በአገርና በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስመዝገብ እየሰራ ነው፡

የሸዋል - ኢድ በዓል የኢድ አልፈጥር በዓል ከተከበረበት ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት ከተፆመ በኃላ ከስድተኛው ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ ማግስቱ 10 ሰዓት ድረስ የሚከበር ነው።
በዓሉን የሐረሪ ብሔረሰብ ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው የሚያከብሩት ሲሆን  ቱሪስቶችና ሌላውም የህብረተሰቡ ክፍልም በዓሉ በሚዘጋጅበት ጀጎል ድረስ በመሄድ በአንድነት ያከብሩታል ።

በተለይ ደግሞ ወጣቶች የሚተጫጩበት መልካም አጋጣሚ ተደርጎም ይወሰዳል ።
የዘንድሮው የሸዋል ኢድ በዓል እንዳለፉት ጊዜያት በአደባባይና በአንድነት ሳይሆን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሁሉም በየቤቱ ሆኖ እንዲያከብረው ተደርጓል ።

በክልሉ በሚገኘው የጨለንቆ ሰማዕታት አዳራሽ የተለያዩ አድባራት ዛኪሮች ተገኝተው ርቀታቸውን በመጠበቅና ከንክኪ ነጻ በመሆን ውዳሴ አድርሰዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ሀጂ መሀመድ ሐሺም በሰጡት አስተያየት “በዓሉ የሐረሪዎችንና የሐረርን እሴት የሚሳይ በመሆኑ ሁሉ ጊዜ  በድምቀት አከብረዋለሁ” ብለዋል ።

በዓሉ በክልሉና በሐረሪ ብሔረሰብ በድምቀት ሲከበር በውጭና በሀገር ውስጥ የሚገኙትን በማሰባሰብ ዘመድ ከዘመድ ወዳጅ ከወዳጅ የሚገናኝበት መሆኑን ጠቅሰው የዘንድሮውን ግን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በዓሉን በቤት ውስጥ እንዲከበር መደረጉን አስረድተዋል ።
 “በዓሉ በሚያዘው መሰረት የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሐረሪዎች በቫይረሱ ምክንያት ተጽዕኖ ለደረሰባቸው አቅመ ደካሞችን ይረዱበታል ። ጥላቻ ይወገዳል ። አንድነትና አብሮነት ይጎለብታል“ ብለዋል ።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በዓሉን በጀጎል በአንድነት ባያከበርም ለኔ ልዩ ቦታ ስላለው በግሌ እያከበርኩት እገኛለሁ ያለው ደግሞ ወጣት መሀመድ ዩስፍ ነው።


የዘንድሮም በዓል በተለይ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የጀመርነውን ርቀትን በመጠበቅ፣የመንግስትንና የጤና ባለሞያዎችን ምክር በመተግበርና ለአቅመ ደካሞች ማዕድ በማጋራት እያከበርነው እንገኛለን ብሏል ።

አቶ አብዱራህማን መሀመድ የተባሉ የብሔረሰቡ አባል በበኩላቸው የዘንድሮው የሸዋል ዒድ በአለም አቀፍና በአገራችን የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በተናጥል እንድናከብር አድርጎናል ባይ ናቸው ።

የክልሉ የባህል ፣ ቅርስና ቱሪዝብ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲኒር ረመዳን እንደገለፁት ሸዋል ኢድ በዓል የሐረሪ ብሔረሰብ ለበርካታ ዓመታት ሲያከብረው ኖሯል ።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ መጥተው የሚያከብሩት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበትና የእርስ በርስ ግንኙነቶችን የሚያጎለቡትበት ቢሆንም ዘንድሮ ግን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በዓሉ በቤት ውስጥ እንዲከበር መደረጉ ተገቢ ነው ብለዋል ።


የክልል መንግስት በክልሉ የሚገኘውን እና በማይዳሰስ ቅርስነት የሚታወቀውን የሸዋል ኢድ በዓልን በአገርና በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም