የምክር ቤቱ አባላት የተገኘው የሰላምና የአንድነት ለውጥ እንዲቀጥል ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ለመስራት ተዘጋጅተዋል

62
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 በአገሪቱ የተገኘውን የሰላምና የአንድነት ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከመረጣቸው ህዝብ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ። አባላቱ ወደ ተመረጡበት አካባቢ ሲሄዱ በአገሪቱ የተገኘው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት የበለጠ ማጎልበት ቀዳሚ ስራቸው እንደሚሆን ገልጸዋል። የተጀመረው የሰላምና የአንድነት ጉዞ እንዲጠናከርና በተለያየ መልኩ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በየደረጃው እንዲፈቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባባር እንደሚሰሩ የተናገሩት የምክር ቤት አባል አቶ ዱቤ ጂሎ ናቸው። በተጨማሪ በመንግስት የተጀመሩ የልማትና የኮንስትራክሽን ስራዎች ምን ደረጃ ላይ እንደደረሱና የሚገጥሟቸው ችግሮች ከቀበሌ እስከ ምክር ቤት ድረስ በየደረጃ እንዲፈቱ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ተስፋዬ አበራ እንዳሉት የህብረተሰቡ አንድነትና ሰላም ሲከበር የሌሎችን መብት በማይጥስ መልኩ መሆን እንዳለበት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በተለይ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና ህብረተቡ የሚጠይቃቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከህብረተሰቡ ጋር እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ እንዳሉት “አሁን የተገኘውን ለውጥ እንዲቀጥል እንደ ምክር ቤት አባላት በሄድንበት አካባቢ ህብረተሰቡ የለውጡ አጋዥ እንዲሆንና እኛም የሚጠበቅብንን ለመወጣት እንሰራለን” ብለዋል። የተጀመሩ የሰላምና የአንድነት ለውጦች በጅምር ላይ ያሉ በመሆናቸው ህብረተሰቡን አሳምነው ለውጡ ቀጣይ እንዲሆን እንደሚሰሩ ወይዘሮ ቸርነት ሃይለማርያም ገልጸዋል። በተለይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱና ህዝቡ በጋራ እንዲዋጋቸው በየአደረጃጀቱ ካሉ አመራሮች ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም