የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በደባርቅ የሚስገነባው ትምህርት ቤት እየተፋጠነ ነው

85

ጎንደር፣ ግንቦት 23/2012 (ኢዜአ)በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በ14 ሚሊዮን ብር በደባርቅ ከተማ እየተገነባ ያለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመጪው የትምህርት ዘመን አገልግሎት መሰጠት እንደሚጀምር የከተማው ትምህርት ፅህፈት ቤት ገለፀ ።

በደባርቅ ከተማ ቁልጭ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠው ግንቦት 24 ቀን 2011ዓ.ም ነበር፡፡

የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተመስገን ፈንታ ለኢዜአ እንደተናገሩት የትምህርት ቤቱ የግንባታ ደረጃ በአሁኑ ወቅት 65 በመቶ ተጠናቋል፡፡

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ እያንዳንዳቸው 40 ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ 18 የመማሪያ ክፍሎች እንዳሉት ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም 3 ቤተ-ሙከራዎችና አንድ ቤተ-መጻህፍት፣ የእደ ጥበብ ማእከል፤ የመምህራን ማረፊያ የርእሰ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች መገልገያ ቢሮዎችንና ሌሎች ክፍሎችን የያዘ ነው፡፡

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የሚውል 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ፈቅዶ መስጠቱን የገለጹት ሃላፊው፤ ግንባታው 250 ለሚደርሱ የጉልበት ሰራተኞች ጊዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል ።

በሁለት ፈረቃ ከ1 ሺህ 400 በላይ የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ትምህርት ቤቱ በ2013 ዓ/ም አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለዋል፡፡

የደባርቅ ከተማ ነዋሪ አቶ ውቤ በዛብህ በሰጡት አስተያየት በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ግንባታው በመካሄድ ላይ የሚገኘው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ በመማሪያ ክፍል ጥበት ለተቸገሩ ልጆች እፎይታ የሚሰጥ ነው፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የትምህርት ቤቱን የግንባታ መሰረት ድንጋይ ሲያስቀምጡ ደስታ ተሰምቶን ነበር ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ደሳለኝ ማሞ ና፤ቸው ።

ግንባታው ተፋጥኖ በማየታችን ደግሞ ደስታችን እጥፍ ድርብ ሆኗል ብለዋል ።

በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የአዘዞ ሎዛ ማርያም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቆ በዚህ ዓመት መግቢያ  የመማር ማስተማር ስራው መጀመሩ ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም