የተቋረጠውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ለማስቀጠል በቴክኖሎጂ የታገዘ እንቅስቃሴ ተጀምሯል

75

አዲስ አበባ, ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተቋረጠውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ለማስቀጠል በቴክኖሎጂ የታገዘ እንቅስቃሴ መጀመሩን የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ''የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በዘመነ ኮቪድ'' በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ የቪዲዮ ፓናል ውይይት አካሂዷል።   

በውይይቱ ላይ የዘርፉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ሲሆን ዘርፉ በወረርሽኙ ምክንያት የተጋረጠበት ፈተናዎች፣ የመፍትሔ ሀሳቦችና የአገራት ተሞከሮዎች ተዳሰውበታል።  

የሣይንስና ከፍትኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በበርካታ መስኮች ጥላ ያጠላ ቢሆንም በትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ግን የጎላ ጫና አሳድሯል።

በተለይም ቴክኒክና ሙያ 70 በመቶ የተግባር ሥልጠና መሆኑ ለትምህርት አሰጣጡ የበለጠ ማነቆ መሆኑን ገልጸው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሠልጣኝ ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት የቴክኖሎጂ አማራጮችን መጠቀም መጀመሩን ተናግረዋል።  

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ ሚኒስቴሩ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት በኔትወርክ እንዲተሳሰሩ የማድረግ ሥራዎችን ጀምሯል።

በአሁኑ ወቅትም የቴክኒክና ሙያ የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት መደራጃቱን የጠቆሙት ሚኒስትሯ ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን ሚኒስቴሩ የአሥር ዓመት የዲጂታል ስኪል መሠረተ ልማት የድርጊት መርሃ ግብር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።   

''ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን የቴክኒክና ሙያ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በዓለም ባንክ የሚደገፍ ፕሮጀክት ወደ ሥራ እየገባ ነው'' ያሉት ፕሮፌሰር ሒሩት፣ ይህም ቴክኖሎጂን በዘርፉ ለማስፋፋት የሚያግዝ እንደሆነ አብራርተዋል። 

የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው "በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተሟላ አይ.ሲ.ቲ መሠረተ ልማት አለመኖር ትልቅ ጫና ፈጥሯል" ብለዋል።

ችግሩን ለማቃለል እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ለተማሪዎች የመማሪያ ግብአቶችን ማሰራጨታቸውን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታው፣ ይህ አካሄድ ለሁሉም አካባቢዎች ከአቅም አንጻር የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።  

ይሄንን ችግር ለማቃለለም ሚኒስቴሩ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለተማሪዎች የሚሰጡትን የትምህርት ይዘት ወደ መረጃ ቋት ማዕከል በማስገባት ለተማሪዎቻቸው እንዲያደርሱ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ጠቅሰዋል።

ዶክተር ሙሉ እንደሚሉት በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ በአሰልጣኞችም በሠልጣኞም ዘንድ የአቅም ክፍተት መኖሩ የተለየ ሲሆን ክፍተቱን ለመሙላትም የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተ ግብረ ኃይል መቋቋሙን አመልክተዋል።   

ግብረ ኃይሉ በሁለት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ ለማስገባት እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ሲሆን፣  በዋናነት ግብረ ኃይሉ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሚያስፈልጉ ላፕቶፖች፣ ሞባይሎችና ታብሌቶችን ማዳረስ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።  

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ500 ሺህ በላይ የቴክኒክና ሙያ ሠልጣኞች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ሲሆን ከ1 ሺህ 600 መቶ በላይ ደግሞ ማሰልጠኛ ተቋማት እንዳሉ የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም