በነገሌ ከተማ በግብርና ምርቶች ላይ የተደረገው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ

58

ነገሌ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) በነገሌ ከተማ የግብርና ምርቶችና ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የተደረገው ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው በከተማው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

የተጋነነ ዋጋ በመጨመር ሕዝብን ለማማረር የሚሰሩ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እየሰራ መሆኑን የከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አዳነች ገሠሠ በሰሞኑ ገበያ በዋና ዋና የግብርና ምርቶች ላይ በኪሎ ከ5 እስከ 15 ብር የዋጋ ጭማሪ መደረጉን እንደታዘቡ ተናግረዋል።

ዋጋ ከጨመሩት መካከል የምግብ ዘይት፣ ቀይና ነጭ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ካሮት፣ ጤፍ፣ ሎሚ፣ ድንችና ጎመን እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ሸማቹ እንዳይጎዳ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ቢባልም የግብርና ምርቶች በየቀኑ ዋጋ ተጨምሮባቸው ለገበያ እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።

ወይዘሮ አመለወርቅ ክፍሌ በበኩላቸው የአሁኑ የዋጋ ጭማሪ እየተጋነነ መጣ እንጂ በበዓላት ወቅት ያለምንም ምክንያት የዋጋ ጭማሪ መደረጉ የተለመደ እንደሆነ አስታውሰዋል።

በሁሉም የገበያ ቀናት ለሸመታ ሲወጡ እንደታዘቡት ዋጋ ያልጨመረ የግብርናና የሸቀጣ ሸቀጥ ምርት እንደሌለ መታዘባቸውን አመልክተዋል፡፡

"የኮሮና ቫይረስ ሥጋት ሳያንስ ዋጋ በመጨመር የኑሮ ውድነት እንዲባባስ የሚሰሩ ነጋዴዎች ተግባር  ያሳዝናል" ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ አበባ መኮንን ናቸው።

ቀደም ሲል በኪሎ 18 ብር የነበረውን ቀይ ሽንኩርት 33 ብር፣ 13 ብር የነበረውን ቲማቲም 25 ብር፣ 140 ብር የነበረውን በርበሬ 180 ብር፣ 32 ብር የነበረውን ጤፍ 38 ብር  መድረሱን ጠቁመዋል።

ሃይ ባይ ያጡና እንደፈለጉ የሚሰሩ ነጋዴዎች ላይ የሚመለከተው አካል ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ገበያውን እንዲያረጋጋ መፈለጋቸውንም ገልጸዋል።

በከተማው በቀይ ሽንኩርት ንግድ የተሰማሩት አቶ መሀመድ አብዱላሂ "ገበሬው በምርቱ ላይ ዋጋ ሲጨምር እኛም ጨምረን እንሸጣለን" ብለዋል።

የአሁኑም የዋጋ ጭማሪ ምርቱ ከሚገዛበት ቦታ ስለጨመረ እንጂ ከወትሮው የተለያ ትርፍ ለማግኘት ተብሎ የተደረገ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የነገሌ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቦነያ ቱርቃ የተጋነነ ዋጋ የጨመሩ 30 የንግድ ድርጅቶች ታሽገው ባለንብረቶቹን የሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተጋነነ ዋጋ በመጨመር ማስረጃ የቀረበባቸው ሁለት ነጋዴዎች ደግሞ ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑንም አመልክተዋል።

ምክንያት ሳይኖር በኮሮና ቫይረስ ሰበብ ዋጋ የጨመሩ ነጋዴዎች ድርጅት ታሽጎ ፈቃዳቸው ይሰረዛል፣ የገንዘብ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም