የአዲስ አበባ በጎፈቃድ ወጣቶች ማኅበር ኮቪድ-19 የመከላከል ሥራ አጠናክሮ እንደሚሰራ ገለጸ

115

አዲስ አበባ፤ ግንቦት22/2012 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ እጅ የማስታጠብ ንቅናቄ፣ ሀብት የማሰባሰብና ለተጎዱ ወገኖች ለመድረስ እየሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ በጎፈቃድ ወጣቶች ማኅበር አስታወቀ።

የበጎፈቃድ ማኅበር አመራር አባል ወጣት ዮናስ ምትኩ ተቀዛቅዞ የነበረው የእጅ ማስታጠብና ቫይረሱን የመከላከል ሥራ አጠናክሮ ለመቀጠል ፕሮግራም መንደፋቸውን ገልጿል።

የእጅ ማስታጠቡን ተግባር ለማስቀጠል ከዚህ በፊት ከነበሩት በተጨማሪ የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከሮችና የንጽሕና መጠበቂያ ሣሙናዎች መዘጋጀቱን ተናግሯል።

ከኮቪድ-19 መከላከል ጋር ተያይዞ መጀመሪያ በመደናገጥ በዘመቻ መልክ ተጀምሮ በኋላ ላይ ግን በመላመዳችን የመፋዘዝ ሁኔታዎች መታየቱን የገለጸችው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የበጎፈቃድ ወጣቶች አስተባባሪ ፀሐይ ደምሴ  ነች።

ከዚህ በፊት በአደባባይ ላይ የእጅ ማስታጠብ ፕሮግራም፣ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ፣ ለማኅበረሰብ ማስክ እንዲጠቀም፣ ርቀቱን ጠብቆ እንዲቀሳቀስና እንዳይጨባበጥ፣ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስተባባሪዋ ፀሐይ ደምሴ አስረድታለች።

ይሁንና በመፋዘዛችን ወረርሽኙ ከቀን ወደ ቀን እየተስፋፋ በመምጣቱ በወረዳ ደረጃ ችግሩን ለመፍታት ዕቅድ መንደፋቸውን አስተባባሪዋ ገልጻለች።

ኅብረተሰቡ ማስክ እንዲጠቀም፣ ርቀቱን በመጠበቅ ራሱንና ሌሎችን ከዚህ ወረርሽኝ እንዲታደግ የቅስቀሳ ፕሮግራሙን ከአዲስ አበባ በጎ ፈቃድ ወጣቶች ማኅበር ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በከፋ ችግር ላይ ያሉ ወጣቶችን ከጎናቸው መሆኑን ለማሳየት ከ50 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለ57 ሰዎች የምግብ ድጋፍ ማድረጉን የአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 10 የወጣቶች ማዕከል አስታውቋል።

ዕርዳታውን ያገኙት ወጣቶች ምንም ቤተሰብ ለሌላቸውና አሁን በኮቪድ-19 ምክንያት ከሥራቸው ተፈናቅለው ቤታቸው ለተቀመጡ ወጣቶች መሆኑን የወጣት ማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ገልጿል።

የእጅ ንጽሕናን ለመጠበቅ የማስታጠብ ንቅናቄ መጀመሪያ ላይ የነበረንን ሥነልቦና ከአዲስ አበባ በጎፈቃድ ማኅበር ጋር አጠናከረው የሚሰሩ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም