ለሕዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ በባሕርዳር የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ

61

ባሕርዳር፣ ግንቦት 22/2012  ( ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲያደርጉ የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በባሕርዳር ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ።

ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለተከታታይ ዓመታት በወር ደመወዛቸው ቦንድ በመግዛት ሲደግፉ መቆየታቸውን ሠራተኞቹ አውስተዋል።

ከሠራተኞቹ መካከል አቶ ገነቱ ጥሩነህ እንዳሉት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷ የሆነው የዓባይ ወንዝ ለዘመናት ወደ ባዕድ አገር በመፍሰስ ሲባክን ኖሯል።

ትውልዳቸው የዓባይ ወንዝ በሚያልፍበት አካባቢ በመሆኑም አፈሩን፣ እንጨቱንና ሌላውን የተፈጥሮ ሀብት እያጓጓዘ በመውሰድ ለሱዳንና ግብፅ  ሲሣይ በማድረጉ ሲቆጫቸው መኖሩን አመልክተዋል።

ጊዜው ደርሶ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመሩ ለሀገሪቱ ሕዝቦች ብልፅግናና ቀጣይነት ያለው ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ብርሃን እንዲፈነጥቅ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

እሳቸው ግድቡ ሲጀመር በነበራቸው ከፍተኛ መነሳሳት የወር ደመወዛቸውን በዓመት ለመለገስ ወስነው በኋላ ወደ ቦንድ እንዲቀየር በመወሰኑ እስካሁን 30 ሺህ ብር የሚጠጋ ቦንድ ግዥ በመፈጸም አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ቦንድ በመግዛትና በ8100 መልዕክት በመላክ በገንዘብ ከመደገፍ ባሻገር በችግኝ ተከላና በግድቡ ዙሪያ የሚነሱ አሉታዊ አስተሳሰቦችን ለመመከት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የሀገራችን ሕዝብም ግድቡ ሲጀመር ያሳየውን ከፍተኛ መነሳሳት፣ አንድነት፣ መቻቻልና በጽናት መቆም አሁን ላይ  በግድቡ የውኃ ሙሌት ወቅትም በመድገም እንደ ግብፅ ያሉ ተፅዕኖን መመከት አለበት ብለዋል።

አቶ ገነቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ለማንኛውም ስትኖር መሆኑን በማመን በዚህ ወቅት በአንድነት በመቆም የሀገርና የሕዝብ አለኝታነታቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሌላው የመንግሥት ሠራተኛ  አቶ አሸናፊ ሥዩም በበኩላቸው "ለዘመናት እኛ ኢትዮጵያውያን የዓባይ ወንዝ ያለውን ፀጋ መጠቀም ቀርቶ ያለንን ሀብት እያጓዘ በመኖሩ የዘመናት ቁጭት ሆኖብን ዘልቋል" ብለዋል።

"ግድቡን ገንብተን ካጠናቀቅን ልክ እንደ አድዋ ድል በዓለም ፊት በኩራት የምንቆምበት ይሆናል" ብለዋል።

ይህ ትውልድ በጋራና አንድነት መንፈስ በጽናት በመሰለፍ የግድቡን ግንባታ በማጠናቀቅ በዓለም አደባባይ አንገቱን ቀና በማድረግ በኩራት የሚራመድበት ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።

"ለግድቡ ስኬትም ባለፉት ዓመታት የወር ደመወዜን እየከፈልኩ ግድቡ አሁን ውኃ ከሚሞላበት እንዲደርስ የራሴን አሻራ አስቀምጫለሁ የሚል አስተሳሰብ አለኝ" ብለዋል።

ኅብረተሰብ ግድቡ በባለቤትነት መንፈስ ለማጠናቀቅ የመንግሥትን ቅስቀሳ ሳይጠብቅ በገንዘቡ፣ ዕውቀቱና ባለው አቅም ሁሉ አስተዋጽኦ በማድረግ በኩራት ለመጓዝ በአዲስ መልክ መነሳሳት እንዳለበትም አመልክተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ 73 በመቶ በመድረሱና በመጪው ሐምሌ የውኃ ሙሌት የሚጀመርበት በመሆኑ የተጠናከረ ትብብርና ድጋፍ የሚያስፈልግ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም