በሐረሪ ክልል አተትን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች ተሰርተዋል

90
ሐረር ሰኔ 29/2010 በሐረሪ ክልል የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የሕብረተሰብ የጤና አደጋና ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ቢኒያም ተሾመ ለኢዜአ እንደተናገሩት በክልሉ የክረምት ዝናብን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታን ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። ከመንግስት የጤና ተቋማት በተጨማሪ 89 ለሚሆኑ የግል ሕክምና መስጪያ ጤና ተቋማት ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የአተት በሽታን  በጋራ ለመከላከል ጥረት ተደርጓል። ጤናን አስመልክቶ በክልሉ በሚዘጋጁ የተለያዩ መድረኮችም ለአመራሩና ለሕብረተሰቡ ተወካዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን አመልክተዋል። በአካባቢና በግል ንጽህናን ክፍተት፣ ምግብን አብስሎ ባለመመገብና  እጅን በአግባቡ ካለመታጠብ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ አተትና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይም ቤት ለቤት በመሄድ በጤና በባለሙያዎች ትምህርት መሰጠቱንም ተናግረዋል። ከእዚህ ጎን ለጎን ለሕክምና ወደጤና ተቋም ለሚመጡ ሰዎች በጤና ተቋማት ውስጥ ትምህርት እንዲያገኙ በመደረግ ላይ መሆኑን አብራርተዋል። በገጠር ቀበሌ በሚገኙ ወንዞችንና ኩሬዎች ላይ ኬሚካልን በመጠቀም የማከምና ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ያቆረ ውሃን የማዳረቅ ሥራ በየወረዳው መከናወኑንም አቶ ቢኒያም ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ በ2009 ዓ.ም የክረምት ወቅት ከሐረርና ከአጎራባች ክልል 123 ሰዎች በአተት በሽታ ተይዘው በሕክምና ድነዋል። ባለፈው ዓመት በክልሉ የአተት በሽታ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል የአሚር ኑር ወረዳ አንዱ ነው። በወረዳው የአሚር ኑር ጤና ጣቢያው ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ ሳሊህ እንደሚናገሩት ከወረዳውና ከአጎራባች ክልል 90 ሰዎች በበሽታው ተይዘው በጤና ጣቢያው ሕክምና ተደርጎላቸው ከበሽታቸው መዳናቸውን ገልጸዋል። ዘንድሮም በክልሉ እየጣለ ያለውን ዝናብ ተከትሎ አተት ቢከሰት ሕሙማን ተለይተው የሚታከሙበት ቦታ ከወዲሁ መዘጋጀቱን ገልጸው እስካሁንም በበሽታው ተይዞ ወደጤናጣቢያው የመጣ ሰው አለመሮሩን ተናግረዋል። የአሚር ኑር ወረዳ ጤና ኤክስቴንሽን አስተባባሪ ወይዘሪት ዘመናይ ታምሬ በበኩሏ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በመድረሱ ሰዎች አጥበው እንዲጠቀሙና ጥሬ ስጋን አብስለው እንዲመገቡ የማስገንዝብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጻለች። በአካባቢው ያለውን የምንጭና የኩሬ ውሃን በየጊዜው በኬሚካል በማከም ሕብረተሰቡን ከበሽታው የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግራለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም