በግብርናው ዘርፍ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተስፋ ሰጭ ነው

53

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በግብርናው ዘርፍ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጭና የሚበረታታ መሆኑን አትሌቶችና አርቲስቶች ተናገሩ።

በርካታ አትሌቶችና አርቲስቶች በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በወጣቶች እየተከናወኑ ያሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶችን ጎብኝተዋል።

ከጎብኝዎቹ መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አትሌቶችና  አርቲስቶች  የወጣቶችን  ተጠቃሚነት እውን ለማድርግ የክልሉ  መንግሥት  የጀመረውን  ሥራ አድንቀዋል።

ወጣቶች በተለይ በገጠሩ አካባቢ ያለውን ዕውቀትና ጉልበት ተጠቅመው በልማት ሥራ ላይ በስፋት መሳተፋቸውም ጥሩ ጅምር መሆኑን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በማገዝ ከድህነት ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከር ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

ከአስተያየት ሰጭዎቹ መካከል አርቲስት ሃቢብ ከማል  እንዳለው  በአሁኑ  ጊዜ ወጣቱ  ትውልድ ወደ ልማት መግባቱ ለራሱም ሆነ ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ሚና አለው።

ኢትዮጵያ በርካታ የተማሩ ወጣቶችና  ሰፊ የመሬት ሀብት ያላት በመሆኗ ወጣቶች  ሥራን ከመንግሥት ከሚፈልጉ ይልቅ ያላቸውን ዕውቀትና ጉልበት በመጠቀም ማመረት ይኖርባቸዋል ብሏል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን በወጣቶች በመልማት ላይ ባሉት የፍራፍሬ ምርቶች እንደተደሰተም ተናግሯል።

አትሌት ኢብራሂም ጄይላንም ወጣቱ ትውልድ ወደ ሥራ ገብቶ ራሱን ለውጦ ማየት የረጅም ጊዜ ህልሙ እንደነበር ተናግሯል፡፡

በሥራ ምክንያት ውጭ ሀገር በኖረባቸው ዓመታት የተመለከታቸውን የግብርና ሥራዎች በሀገሩ ተግባራዊ ሆኖ በመመልከቱ መደሰቱን ገልጿል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን የወጣቶች የልማት ተሳትፎም ተስፋ ሰጭ መሆኑን ተናግሯል።  

በሪዮ ኦሎሚፒክ ለሀገሩ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ፈይሣ ሌሊሣ በበኩሉ በወጣቶች እየለሙ የሚገኙ ሥራዎችን በአካል በመመልከቱ መደሰቱን ተናግሯል።

ከዘርፉ ወጣቶች የሚያገኙትን ገቢ በመስማቱና የወጣቶች ሕይወት እየተለወጠ እንደሆነ መመልከቱንም ተናግሯል፡፡

ሌሎች ወጣቶችም ከእነዚህ ወጣቶች ልምድ በመቀመር በየአካባቢያቸው ተመሣሣይ ሥራ እንዲያከናውኑ መክሯል።  

የክልሉ መንግሥት አርሶ አደሩን በመደገፍ ረገድ እያከናወነ ያለው ተግባርም የሚያስመሰግን መሆኑ ተገልጿል።

ይኸው ተግባርም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አትሌቶቹ ጠቁመዋል።

በሳምንቱ በርካታ አትሌቶችና አርቲስቶች በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን  የተለያዩ  የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም