በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለ37 ሚሊዮን ሰዎች ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ግንዛቤ አስጨብጠዋል-ሚኒስቴሩ

49

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለ37 ሚሊዮን ሕዝብ ግንዛቤ ማስጨበጣቸውን የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሥራው ከሁለት ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሰማርተዋል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት እየታየ ቢሆንም፤ቸልተኝነትና መዘናጋት በሽታውን ይበልጥ እያስፋፋው ለመሆኑ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሺህ መብለጡ  ማሳያ ነው።

የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ እንደገለጹት ወረርሽኑ ከተከሰተ አንስቶ በጎ ፈቃደኞቹ ኅብረተሰቡ ከቫይረሱ እንዲጠበቅ ትምህርት ሰጥተዋል።

ኮቪድ- 19 ወደ አገሪቱ ከገባ በኋላ በሚኒስቴሩና በአጋር አካላት  በቅንጅት በተከናወኑት የመከላከልና የማስተማር ሥራዎች ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ቫይረሱ በወጣቶች ላይ እያሳደረ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ለመረዳት ጥናት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ጥናቱ ችግሩን በመለየት የመከላከል ሥራዎች ለማከናወን ያግዛል ብለዋል።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሽታውን ለመከላከል የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።

ለዚህም የሚመለከታቸው የመንግሥትና የግል ተቋማት ለወጣቶቹ ድጋፍ እንዲያደርጉ ወይዘሮ ሕይወት ጠይቀዋል።

ኅብረተሰቡ ቫይረሱን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባሩ ግቡን እንዲመታ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን መመሪያዎችን ማክበር ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም